የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ሴራን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ

You are currently viewing የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ሴራን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ እንደሚቀጥል የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አስታወቁ

AMN- ጥር 3/2018 ዓ.ም

የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ሴራን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) አስታውቀዋል፡፡

የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል ሴራ በሀላባ ቁሊቶ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡

በምሐ-ግብሩም የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ ኢትዮጵያ በብዝሃነት የደመቀች ምድረ ቀደምት ሀገር ነች ብለዋል።

ሀገሪቱ ካሏት ቱባ ባህሎች መካከል አንዱ የሀላባ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ሴራ” መሆኑን ጠቁመው፣ በዓሉን ለትውልድ ለማስተላለፍ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በብዙ ተስፋዎች የተከበበች መሆኗን እና ብዝሃነትን በማክበር ህብረብሔራዊ አንድነትን ለመገንባት በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

የጋራ ትርክትን ለመገንባት የሚደረገው ጥረት ላይ ሁሉም ሊሳተፍ እንደሚገባ የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳደሩ፣ የተጀመረው የብልጽግና ጉዞ ተግቶ መስራትን የሚሻ ነው ብለዋል።

የኢፌዴሪ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ድዔታ ወ/ሮ ነፊሳ አልመሀዲ፣ የሀላባ ሴራ መደገጋፍን፣ አብሮነትንና አንድነትን የሚያጠናክር ባህል መሆኑን ገልጸዋል።

ባህላዊ ሀብቶችን በማጎልበት ሀገራዊ ብልጽግናን ለማምጣት በትኩረት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ሚኒስትር መስሪያ ቤቱም የዘርፉን ሀገራዊ ፋይዳ በመረዳት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ እንደሚገኝ እና እነዚህን ስራዎች አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አክለዋል።

የሀላባ ዞን አስተዳደር አቶ ሙዲን ሁሴን፣ የሀላባ ብሔረሠብ የራሱ ቋንቋ እና ባህል እንዲሁም የዳበረ እሴት ባለቤት መሆኑን ገልጸዋል።

የሀላባ ሴራ ማለት ብሄረሰቡ የሚተደዳርበት ባህለዊ ህግ ወይም ደንብ መሆኑን አቶ ሙዲን ተናግረዋል።

በሀላባ ሴራ ውስጥ የፀደቁ ዋና ዋናዎቹ የዘመን መለወጫ ሴራ፣ የኦገቴ ሴራ፣ የእድሜ ሽግግር (ነቀታ)፣የእናቶች ቃላ፣ የወጣት ወንዶችና ሴቶች ባህላዊ ጨዋታ(ያካ)፣ የጋብቻ፣ የለቅሶ፣ የልጅ አስተዳደግ፣ የማዕረግ ስም አሰጣጥ፣ የመረዳዳት ስርዓት (ሚሻላ)፣ የቤት አሳራር፣ የስም አወጣጥ፣ የልጅ አስተደደግ፣ የጊዜ አቆጣጣር እና የአብሮነትና የሰላም ሴራ ናቸውም ብለዋል።

ባለፉት ዓመታት በዞኑ የነዋሪውን ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውንም አስተዳዳሪው ጠቁመዋል።

ከነዚህ የልማት ስራዎች መካከል በ461 ሚሊየን ብር የተገነባው የሀላባ ዞን አስተዳደር ህንጻ እና በህዝብ ተሳትፎ የመጀመሪያው ምዕራፍ በ633 ሚሊየን ብር የተገነባው የሀላባ ስታዲየም የሚገኙበት መሆኑንም ገልጸዋል።

የሀላባ ስታዲየም ሁለተኛው ምዕራፍ ግንባታ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጀመራልም ብለዋል።

በሀብታሙ ሙለታ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review