በሞሮኮ አስተናጋጅነት እየተከናወነ የሚገኘው 35ኛው የአፍሪካ ዋንጫ ዛሬ የፍፃሜ ተፋላሚዎቹን ይለያል፡፡ ምሽት 1 ሰዓት ላይ ሴኔጋል ግብፅን ትፋለማለች፡፡
ግብፅ ለፍፃሜ ተጠበቀችውን ኮትዲቯር ፣ ሴኔጋል ደግሞ ማሊን በማሸነፍ ነው ለግማሽ ፍፃሜ የበቁት፡፡ ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫው ሲገናኙ የዛሬው ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም በነበረው አምስት ግንኙነት ሁለት ሁለት ጊዜ ድል አድርገዋል፡፡ ለመጨረሻ ጊዜ በተገናኙበት 2021ዱ የፍፃሜ ጨዋታ ሴኔጋል በመለያ ምት አሸንፋ ለመጀመሪያ ጊዜ የአፍሪካ ዋንጫ ማንሳቷ ይታወሳል፡፡
ዛሬ ምሽት 1 ሰዓት በስታድ ኢብን ባቱታ በሚደረገው ጨዋታ ግብፆች ከአራት ዓመት በፊት የደረሰባቸውን ሽንፈት ለማስረሳት ይፋለማሉ፡፡ በተለይ በሊቨርፑል የቡድን አጋር የነበሩት ሳዲዮ ማኔ እና ሞሐመድ ሳላህ ፍጥጫም ይጠበቃል፡፡

ምሽት 4 ሰዓት አዘጋጇ ሞሮኮ ከናይጄሪያ ጋር ትጫወታለች፡፡ በበርካታ ደጋፊዎቿ ታጅባ ጥሩ ጉዞ እያደረገች የምትገኘው ሞሮኮ ዛሬ በናይጄሪያ ትፈተናለች፡፡
ሞሮኮ በተፈተነችበት ጨዋታ ካሜሩንን አሸንፋ ስታልፍ ፣ ናይጄሪያ በአስደናቂ ብቃት አልጄሪያን በመርታት ነው ግማሽ ፍፃሜውን የተቀላቀሉት፡፡
ሁለቱ ሀገራት በአፍሪካ ዋንጫ እርስ በእርስ ሲጫወቱ የዛሬው ለስድስተኛ ጊዜ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ባደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ሞሮኮ ሦስቱን በማሸነፍ የበላይነቱን ትወስዳለች፡፡ ናይጄሪያ ሁለቱን ጨዋታዎች ድል አድርጋለች፡፡
የዛሬ ጨዋታ ምሽት 4 ሰዓት ላይ በልዑል ሞሌይ አብደላ ስታዲየም ላይ ይከናወናል፡፡
በሸዋንግዛው ግርማ