ለበለጸገች ኢትዮጵያ ዕውን መሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

You are currently viewing ለበለጸገች ኢትዮጵያ ዕውን መሆን የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ ተጠየቀ

AMN- ጥር 6/2018

በ2030 በአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች የበለጸገች ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ ጥሪ አቅርበዋል።

የሲቪክ ማኅበራት ለኢትዮጵያ ሀገራዊ ልማት ባበረከቱት አስተዋጽዖ ላይ ያተኮረ ዓመታዊ ሲምፖዚየም እየተካሄደ ይገኛል።

በመርሐ ግብሩ ላይ የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሙላቱ ተሾመ (ዶ/ር)፣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ዛህራ ዑመድ፣ የአማራ ክልል ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ፋንቱ ተስፋዬ፣ የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ፥ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል።

ቤዛ ፖስተሪቲ የተሰኘው የልማት ድርጅት የ25ኛ ዓመት የምስረታ በዓሉን ምክንያት በማድረግ “የዛሬ ትጋት ለነገ ውጤት” በሚል መሪ ሀሳብ ባዘጋጀው በዚህ መርሐ ግብር ላይ ነው በሲቪክ ማኅበራት ሚና እና አበርክቶ ዙሪያ ምክክር የተካሄደው።

በመርሐ ግብሩ ላይ የተገኙት የጤና ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር ደረጀ ዱጉማ እንደተናገሩት፣ ቤዛ ፖስተሪቲ የኤች.አይ.ቪ ስርጭትን በመግታት፣ የሴት ልጅ ግርዛትንና መሰል ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶችን በመከላከል ረገድ ከመንግስት ጎን በመሆን ከፍተኛ አስተዋጽዖ አበርክቷል። በ2030 በአፍሪካ ተምሳሌት የሆነች የበለፀገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሚደረገው ጥረት፣ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡም ሚኒስትር ደኤታው አሳስበዋል።

የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ሳምሶን ቢራቱ በበኩላቸው፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች የልማት ክፍተቶችን በመለየትና በመሙላት አበርክቷቸውን አጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።

ከ25 ዓመታት በፊት በኮምቦልቻ ከተማ የተመሠረተው የቤዛ ፖስተሪቲ ሀገር በቀል ድርጅት መሥራችና ዋና ዳይሬክተር አቶ ሰዒድ አሕመድ፣ ድርጅቱ ተደራሽነቱን በማስፋት በጤና፣ በወጣቶች ልማት፣ በማኅበራዊ ጥበቃና ዘላቂ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ላይ በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ገልጸዋል።

የድርጅቱ የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ሆርዶፋ በቀለ ቤዛ ፖስተሪቲ በጤና፣ በወጣቶች ልማት፣ በማኅበራዊ ጥበቃ እና ለችግሮች ሀገር በቀል መፍትሔ ማፈላለግ ላይ አተኩሮ ሲሠራ ከጎኑ ለነበሩ አካላት ምስጋና አቅርበው መንግስት ለሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች ምቹ ምኅዳር በመፍጠር ረገድ የጀመረውን አበረታች ተግባር አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በይታያል አጥናፉ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review