AMN ጥር 15/2018
የኢትዮጵያ አየር ኃይል ፈጣን እድገት ለአፍሪካ ሀገራት አብነት ይሆናል ሲሉ የአፍሪካ ሀገራት ወታደራዊ አታሺዎች ገለጹ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት የኢትዮጵያ አየር ኃይል 90ኛ ዓመት ክብረ በዓልን በማስመልከት የተዘጋጀው የአቬዬሽን ኤክስፖ ተከፍቷል።
ኤክስፖው የወደፊቱን የአቬዬሽን አቅም በጋራ እንገንባ በሚል መሪ ሀሳብ የተዘጋጀ ሲሆን፤ ኤክስፖውን የጎበኙ የተለያዩ ሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ለአፍሪካ ሀገራት ምሳሌ በሚሆን አግባብ በከፍተኛ ፍጥነት እያደገ ስለመሆኑ መታዘባቸውን ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቦትስዋና ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል ሞታሲ ቼሌኒያኔ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል በአቬዬሽን፣ ኢንጂነሪንግና ቴክኖሎጂ ዘርፍ አስደማሚ ለውጥ ውስጥ መሆኑን ከኤክስፖው መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በተለይ አየር ኃይሉ ጥገናን ጨምሮ በሌሎች ቁልፍ የዘርፉ ምህንድስና ስራዎች ራሱን ለመቻል እያከናወነ ያለው ስራ የሚደነቅ መሆኑን አንስተው፤ በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከዚህ ልምድ መውሰድ እንዳለባቸው ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የናሚቢያ ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ማካንዚ ቺቤራ በበኩላቸው እንደገለጹት፤ ባለፉት ጊዜያትም ሆነ አሁን ላይ የኢትዮጵያ አየር ኃይል የራሱን እና የአፍሪካን አቅም ለማሳደግ ጥረት እያደረገ ነው።

የአፍሪካ ሀገራት በጋራ እና በትብብር ከሰሩ ብዙ ርቀት መሄድ እንደሚችሉ ጠቁመው፤ በዚህ ረገድ የኢትዮጵያ አየር ሃይል የወሰደውን ተነሳሽነት አድንቀዋል።
በኢትዮጵያ የጋቦን ኤምባሲ ወታደራዊ አታሼ ኮሎኔል አርሲዴ አንጉሌ፤ የኢትዮጵያ አየር ሃይል ሀገር የሚወክል ታላቅ ተቋም መሆኑን መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል።
ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትም ጥሩ ምሳሌ ነው ብለዋል።