AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም
አዲስ አበባ ስትቆረቆር አረንጓዴ ደኖችና በርካታ ንፁሕ ወንዞች ነበሯት።
በጊዜ ሂደት ግን አረንጓዴ ደኖች እየተጨፈጨፉ፤ ወንዞቿም እየተበከሉ ተፈጥሮአዊ ማንነታቸውን አጥተዉ ወደ መጥፋት ተሸጋገሩ፡፡
ከቅርብ ጊዜ አመታት ወዲህ ግን የአዲስ አበባን ደኖችና ወንዞች ከጥፋት ለመታደግ እና ወደ ቀድሞ ተፈጥሮአዊ ገጽታቸዉ ለመመለስ በተሰሩ በርካታ የልማት ስራዎች አመርቂ ዉጤቶች ተመዝግበዋል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ ለደረቅ ቆሻሻ አያያዝ፤ ለጽዳት፤ለአረንጓዴ ልማት እና ለከተማ ዉበት የሰጠዉ ልዩ ትኩረት የመዲናዋን ገጽታ ከመቀየር አልፎ በአህጉርና አለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ተቀባይነትና እዉቅ አስገኝቶለታል።
በደረቅ ቆሻሻ አስተዳደር በኩል በተሰሩት ስራዎች ቆሻሻን መልሶ መጠቀም፤ ለኮምፖስት ምርት እና ለኃይል ማመንጫ ማዋል ተችሏል፡፡
በዚህም የከተማ አስተዳደሩ አለም አቀፍ እውቅና ያገኘ ሲሆን አዲስ አበባም ከአፍሪካ አስሩ ፅዱ ከተሞች አንዷ ለመሆን በቅታለች፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መሪነት በተጀመረዉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በ2ዐ1ዐ ዓ.ም 2.8 እጅ ላይ የነበረዉን መዲናዋን አረንጓዴ ሽፋን አሁን ላይ ወደ 24 እጅ ማሳደግ ተችሏል፡፡

ባለፉት አምስት አመታት በመዋቅራዊ ፕላኑ መሰረት በ7ሺህ ሄ/ር መሬት ላይ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች የተሰሩ ሲሆን ከ90 ሚሊዮን በላይ ችግኞችም ተተክለዋል፡፡
የተተከሉ ችግኞችን የመንከባከብ ስራም በተቀናጀ መንገድ እየተሰራ ይገኛል፡፡
የከተማ አስተዳደሩ አዲስ አበባን እንደ ስሟ ዉብ አበባ ለማድረግ በኮሪደርና ወንዝ ዳርቻ ልማት ጭምር በሰራቸዉ መጠነ ሰፊ የልማት ስራዎች መዲናዋ ውብ፤ ጽዱ ፤ ማራኪ እና አረንጓዴ ለመሆን በቅታለች፡፡
የከተማ አስተዳደሩ በህገወጥ መንገድ እና በወረራ ተይዘዉ ለነበሩ 266 ቦታዎች ካርታ በማውጣት የአረንጓዴ ቦታዎች የይዞታ ማረጋገጫ እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን በተከታዩ የበጀት አመትም ይህንኑ እርምጃ አጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታዉቋል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ