የተላለፉ መሥሪያ ቦታዎች ለታለመላቸው ተግባር እንዲውሉ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው

You are currently viewing የተላለፉ መሥሪያ ቦታዎች ለታለመላቸው ተግባር እንዲውሉ ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ ነው

AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ አንቀሳቃሾችና አምራች ኢንተርፕራይዞች የተላለፉ የመሥሪያ ቦታዎች ፣ ሼዶችና ሱቆች ለተሰጡበት ትክክለኛ ዓላማ ብቻ መዋላቸውን ለማረጋገጥ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ እየተደረገ እንደሚገኝ የከተማዋ የመሥሪያ ቦታዎች ልማትና አስተዳደር ኤጀንሲ ገልጿል።

የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር አይዳ አወል ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ “አገልጋይ” መሰናዶ ጋር ባደረጉት ቆይታ ፣ የተቋሙ ዋና ዓላማ የመሥሪያ ቦታዎችን ማስተላለፍ ብቻ ሳይሆን፣ ቦታዎቹ በአግባቡ ሥራ ላይ ውለው የዜጎችን ተጠቃሚነት ማረጋገጥ በመሆኑ ጥብቅ የክትትልና የእርምት እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉ ብለዋል።

መመሪያ ተላልፈው በተገኙና ችግር ባለባቸው ላይ የእርምት እርምጃ በመውሰድ መሥሪያ ቦታው ለሌሎች የመስራት ፍላጎት ላላቸው ዜጎች እንዲተላለፍ መደረጉንም ተናግረዋል።

ኤጀንሲው በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከሥራና ክህሎት ቢሮ ፣ ከኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ እና ከከተማ ግብርና ኮሚሽን ጋር በመቀናጀት የመሥሪያ ቦታ ማቅረቡን ዋና ዳይሬክተሯ ገልጸዋል።

በበጀት ዓመቱ በሥራና ክህሎት ቢሮ የተደራጁ ከ3 ሺህ 46 በላይ አንቀሳቃሾች የመሥሪያ ቦታ ማግኘት መቻላቸውን የጠቀሱት ዋና ዳይሬክተሯ አይዳ አወል ፣ ወደ ኢንዱስትሪ ክላስተር የተሸጋገሩ 55 አምራቾች ፣ 28 አዲስ ጥያቄ ያቀረቡ እና 24 የማስፋፊያ ቦታ የጠየቁ አምራች ኢንዱስትሪዎች የቦታ ድጋፍ ተደርጎላቸዋል ብለዋል።

በከተማዋ በተከናወነው የኮሪደር ልማት የተገነቡትን ጨምሮ ደረጃቸውን የጠበቁ ከ 5ሺህ በላይ ሱቆች ፣ 91 ሼዶች እና 4 ህንጻዎች ተጠናቀቀው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸውንም ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review