“አዲስ አበባ በገቢና በፋይናንስ ሀብት አስተዳደር ያመጣችው ስኬት ለአፍሪካ ከተሞች አርዓያ ሆኗል”
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ
የአፍሪካ ከተሞች በፈጣን የህዝብ ቁጥር ዕድገት እና በማህበራዊ አገልግሎት ፍላጎት ጫና ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ወቅት፣ የፋይናንስ አቅምን ማጠናከር ለህልውናቸው ወሳኝ ሆኗል። በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ይፋ ያደረገው ጥልቅ የዳሰሳ ጥናት እንደሚያመላክተው፣ አዲስ አበባ በፋይናንስ አስተዳደር ረገድ ካሳየችው አስደናቂ ለውጥ የተነሳ ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ተሞክሮዋን እንድታካፍል ተመርጣለች።
ይህ ዕውቅና ከተማዋ ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ ምንጮቿን ለማስፋት፣ ገቢዋን በቴክኖሎጂ ለማሳደግ እና ወጪዋን በስርዓት ለመምራት ያደረገችው ጥረት ውጤት ስለመሆኑም ተነግሯል። በአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አማካኝነት በአህጉሪቱ ከተሞች ላይ የተካሄደው ይህ የፋይናንስ አፈፃፀም ዳሰሳ ጥናት በዋናነት ያተኮረው ከተሞች ራሳቸውን በራሳቸው የመቻል አቅማቸው (Financial Sustainability) እና የከተማ ልማት ፋይናንስ ፍላጎታቸውን እንዴት እየሸፈኑ እንደሆነ ለመፈተሽ ነው። በጥናቱ ላይ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ ሌሎች የአፍሪካ ታዋቂ ከተሞች የተሳተፉ ሲሆን አክራ፣ ካዛብላንካ፣ ናይሮቢ፣ ሀርጌሳ እና ኪጋሊን የመሳሰሉ ከተሞች በጥናቱ ተካትተዋል፡፡
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን የከተሞቹን የፋይናንስ ጤንነት እና አስተዳደር ለመመዘን 6 መሠረታዊ መስፈርቶችን ተጠቅሟል፡፡ የገቢ አሰባሰብ ብቃት፣ የበጀት ዝግጅት እና አጠቃቀም፣ የፋይናንስ ግልጽነት እና ተጠያቂነት፣ የብድር እና የዕዳ አስተዳደር፣ የንብረት አስተዳደር እንዲሁም የዲጂታል ፋይናንስ ስርዓትን የተመለከቱ ዋና ዋና መስፈርቶች በመመዘኛነት ተካትተዋል፡፡

አዲስ አበባ ከተመዘነችባቸው ስድስት መስፈርቶች ውስጥ በአምስቱ የላቀ እና አርዓያ የሚሆን ውጤት በማስመዝገብ በአፍሪካ ቀዳሚ መሆን ችላለች። በተለይም በሚከተሉት ዘርፎች የታየው ውጤት ለጥናቱ ባለሙያዎች አስገራሚ ሆኗል፡፡
ከተማዋ የግብር አከፋፈል ስርዓቷን በማዘመን እና አዳዲስ የገቢ ምንጮችን በመለየት ረገድ ካለፉት ዓመታት ከፍተኛ ዕድገት አሳይታለች። የአዲስ አበባ የክፍያ ስርዓቶች ወደ ዲጂታል መቀየራቸው ትልቁን ድርሻ ይዟል። በሌላም በኩል ከተማዋ ግዙፍ ሜጋ ፕሮጀክቶችን ካላት በጀት ጋር አጣጥማ የመምራት ብቃቷ ተመዝኗል። የመሬት ይዞታዎችን እና የመንግስት ቤቶችን ለከተማዋ ገቢ በሚያመነጭ መልኩ የማስተዳደር ስልት እና የከተማዋ የፋይናንስ ሪፖርቶች በየጊዜው ለህዝብ ይፋ መደረጋቸው እና የኦዲት ግኝቶች ላይ የሚወሰዱ እርምጃዎች በስኬት ከተጠቀሱ ጉዳዮች መካከል ይገኙበታል፡፡
አዲስ አበባ በዚህ ጥናት የላቀ ውጤት ማምጣቷ፣ ከተማዋ የዓለም አቀፍ የፋይናንስ ተቋማትን እምነት እንድታገኝ ያደርጋታል። በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን አዲስ አበባን እንደ ተምሳሌት በመምረጥ፣ ሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ከእሷ ምርጥ ተሞክሮ እንዲወስዱ መድረክ አዘጋጅቷል። ይህ ውጤት የሚያሳየው፣ የፖለቲካ ቁርጠኝነት እና የቴክኖሎጂ አጠቃቀም ሲታከልበት፣ የአፍሪካ ከተሞች የውጭ እርዳታ ሳይጠብቁ የራሳቸውን ልማት በራሳቸው ፋይናንስ መምራት እንደሚችሉ ነው። አዲስ አበባ አሁን የአፍሪካ ዲፕሎማሲ ማዕከል ብቻ ሳትሆን፣ የከተሞች የፋይናንስ አስተዳደር ተምሳሌት መሆኗንም አረጋግጣለች።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤም እንደሚገልፁት አዲስ አበባ በገቢና በፋይናንስ ሀብት አስተዳደር ያስመዘገበችው ውጤት ለሌሎች የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ አርዓያ መሆኑን እና ይህ መድረክም የአፍሪካ ከተሞችን የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ የምንቀርጽበት ታሪካዊ አጋጣሚ ነው ብለዋል።
የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት አዲስ አበባ ያስመዘገበችው የልማት ስኬት ሌሎች ከተሞች ተሞክሮ እንዲቀስሙበት የታለመ የውይይት መድረክ በከንቲባ ጽሕፈት ቤት ተካሂዷል፡፡ በዚሁ ወቅት ከንቲባ አዳነች፣ ከተማዋ የግብር አስተዳደርን በማዘመንና በዲጂታል መንገድ በመምራት ረገድ ባመጣችው ለውጥ የራስ ምንጭ ገቢዋን በከፍተኛ ሁኔታ ማሳደግ ችላለች ብለዋል።

በተለይም በንብረት ላይ የተመሠረተ ግብርንና የንግድ ፈቃድ አሰጣጥን በማዘመን የፋይናንስ አቅምን ማሳደግ መቻሉን ከንቲባዋ አብራርተዋል። ይህም የአፍሪካ ከተሞች በማዕከላዊ መንግሥት ድጎማ ላይ ብቻ ከመደገፍ ወጥተው በራሳቸው አቅም ዘላቂ ልማትን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ትልቅ ትምህርት የሰጠ መሆኑ ተመላክቷል። በመድረኩ ላይ የናይሮቢ፣ ዳሬ ሰላም፣ ሉሳካ፣ ኪጋሊ እና ያውንዴ ከተሞች ከንቲባዎች እና ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል፡፡
“አዲስ አበባ አህጉራዊ ኃላፊነቷን በብቃት በመወጣት፣ ለአፍሪካውያን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን የጋራ መማማሪያ መድረክ መሆኗን ዳግም አረጋግጣለች። በተለይም የገቢ እና የፋይናንስ ሀብት አስተዳደርን በማዘመን ረገድ ከተማዋ የጀመረችው ሪፎርም ውጤታማና ለአፍሪካ ከተሞች አርዓያ መሆኑን የጥናቱ ግኝት አመላክቷል። ይህ ስኬት ከተማችን ከምትሰበስበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 71 በመቶውን ለልማት ሥራዎች በመመደብ፣ የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስናደርግ የቆየነው የሪፎርም ጉዞ ውጤታማነት ማሳያ ነው” ሲሉም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ያስረዳሉ።
በከተሞች ታሪክ ውስጥ በጀት ዝም ብሎ ቁጥር ብቻ አይደለም፤ የከተማዋ መሪዎች ለሰው ልጅ ህይወት የሚሰጡት ዋጋ መለኪያ እንጂ። የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን (UNECA) ሪፖርት አዲስ አበባን በአፍሪካ የፋይናንስ አስተዳደር አርዓያ አድርጎ ሲያቀርባት፣ ገዝፎ የወጣው አንድ እውነታ ከተማዋ ካላት አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 71 በመቶውን በቀጥታ ለልማት ስራዎች ማዋሏ ነው፡፡
የከተማ ልማት ባለሙያና የኢኮኖሚ ተንታኞች እንደሚሉት፣ አብዛኞቹ የአፍሪካ ከተሞች ገቢያቸውን የሚጨርሱት ለቢሮክራሲ፣ ለደመወዝ እና ለዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ ወጪዎች ነው። የአፍሪካ ከተሞች የፋይናንስ አጠቃቀምን በተመለከተ፣ አብዛኛው በጀት ለልማት ከመዋል ይልቅ ለዕለት ተዕለት አስተዳደራዊ ወጪዎች እንደሚባክን የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማትና ተመራማሪዎች ጥናት አቅርበዋል።
በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚክ ኮሚሽን በአፍሪካ ከተሞች የፋይናንስ አቅም ላይ ካደረጋቸው ተከታታይ ጥናቶች መካከል “Economic Report on Africa” እና “Financing Sustainable Urbanization in Africa” የተሰኙት ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ ጥናቶች አብዛኞቹ የአፍሪካ ከተሞች ከ80 በመቶ በላይ የሚሆነውን ገቢያቸውን ለደመወዝ፣ ለቢሮ ኪራይ እና ለነዳጅ እንደሚያውሉ ያመላክታሉ።

ዓለም ባንክ “Africa’s Cities: Opening Doors to the World” በሚለው መጽሐፉ እና ተያያዥ ጥናቶቹ የአፍሪካ ከተሞች በ‘ዝቅተኛ የልማት በጀት’ ወጥመድ ውስጥ መውደቃቸውን ይተነትናል። የዓለም ባንክ የከተሞች ልማት ዋና ኢኮኖሚስት ሶሚክ ቪ. ላል በጥናቱ ላይ እንዳሰፈሩት የአፍሪካ ከተሞች ለካፒታል ልማት የሚመድቡት በጀት ከጠቅላላ በጀታቸው ከ20 በመቶ በታች መሆኑን ያሳያል። ይህም ከተሞቹ ‘ውድ ግን ምርታማ ያልሆኑ’ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል።
አዲስ አበባ ግን ይህንን የተለመደ አሰራር ቀልብሳለች። አንዲት ከተማ ከገቢዋ 71 በመቶውን ለልማት ስታውል፣ ውሳኔው ቴክኒካዊ ሳይሆን ሰዋዊ ስለመሆኑ እሙን ነው፡፡ ይህም ማለት ከእያንዳንዱ 100 ብር ውስጥ 71 ብር እናቶች ለሚወልዱበት ክሊኒክ፣ ለአዳጊዎች መጫወቻ ፓርክ እና ለድሆች የሚሆን የዳቦ ፋብሪካዎች ግንባታ እየዋለ ነው ማለት ነው።
ይህ ከፍተኛ የልማት በጀት በከተማዋ ገጽታ ላይ ብቻ ሳይሆን በዜጎች ስነ-ልቦና ላይ ያመጣው ለውጥ ግዙፍ ነው። ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተሰሩት የኮሪደር ልማቶች፣ የአረንጓዴ ስፍራዎች ግንባታ እና የትምህርት ቤት ምገባ ፕሮግራሞች፣ ለነገዋ የሴቶች ተሃድሶና ክህሎት ማበልፀጊያ ማዕከል፣ ጉለሌ የተቀናጀ የልማት ስራ፣ የአረጋውያን ማዕከል እንደዚሁም የመኖሪያ ቤቶች ዕድሳትና ግንባታ ስራዎች የዚሁ የፋይናንስ አጠቃቀም ፍሬዎች ናቸው።
ቀደም ሲል የከተማ ልማት በጥቂት ሰፈሮች ብቻ የተገደበ ነበር። አሁን ግን ይህ በጀት ወደ ሰፈር መንገዶች፣ ወደ ጤና ኬላዎች እና ወደ ህዝብ መጓጓዣዎች ፈሰስ ሆኗል። ለልማት የሚመደበው በጀት ለቆንጆ መንገዶች ብቻ ሳይሆን፣ ለሰው ልጅ ክብር የሚመጥን አካባቢ ለመፍጠር ውሏል። ለምሳሌ፣ የወንዝ ዳርቻ ልማቶች ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ዜጎች ያለ ክፍያ የሚዝናኑባቸው ስፍራዎች ሆነዋል።

በእርግጥ 71 በመቶ ገቢን ለልማት መመደብ ቀላል ውሳኔ አይደለም። ይህንን ለማድረግ የአስተዳደር ወጪን በከፍተኛ ሁኔታ መቀነስ፣ አላስፈላጊ ስብሰባዎችንና ብክነትን ማስቀረት ይጠይቃል። አዲስ አበባ የፋይናንስ አስተዳደሯን ዲጂታላይዝ ማድረጓ፣ ገንዘብ ወደ ግል ኪስ ከመሄድ ይልቅ ወደ ልማት ካዝና እንዲፈስ አስችሏታል። ገንዘብ ማግኘት ብቻ ሳይሆን፣ የተገኘውን ገንዘብ ለብዙሃኑ ዜጋ በሚጠቅም መልኩ መልሶ መመደብ የአዲስ አበባ ትልቁ የብቃት ማረጋገጫ ስለመሆኑ የምጣኔያዊ ሀብት ባለሙያ አቶ ኪሩቤል ሰለሞን ተናግረዋል።
አዲስ አበባ እያስመዘገበች የምትገኘው ሁለንተናዊ ለውጥ ለአፍሪካ ከተሞች ተምሳሌት የሚሆን ነው ሲሉ የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ከንቲባዎች ገልፀዋል፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሲካሄድ የቆየው አህጉራዊ የተሞክሮ ልውውጥ እና የድርጊት መርሃ-ግብር ግምገማ አውደ ጥናት ላይ የተሳተፉ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎችና የስራ ኃላፊዎች ከከንቲባ አዳነች አቤቤ ጋር በመሆን በአዲስ አበባ ያለውን የልማት እንቅስቃሴ፣ የዲጂታል የገቢ አሰባሰብ ስርዓት፣ የከተማዋን የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክቶች እና ሌሎች ሰው ተኮር ስራዎችን ተመልክተዋል።
ከንቲባዎች ከተማዋ ግብር ከምትሰበስብበትና ተግባራትን ከምታከናውንበት መንገድ ሰፊ ልምድ ማግኘታቸውን ተናግረዋል፡፡ ያገኟቸውን ተሞክሮዎች በከተሞቻቸው ተግባራዊ እንደሚያደርጉም ጠቁመዋል፡፡ “በአዲስ አበባ ያየነው የገቢ አሰባሰብ ስርዓትና ገቢ እንዳይባክን የሚደረጉ የፈጠራ ስራዎች የሚደነቁ ናቸው” ብለዋል። አዲስ አበባ ከተማ በሴት ከንቲባ በመመራት አስገራሚ ለውጥ ማምጣቷ በአፍሪካ ሴቶችን ወደ አመራርነት ለማምጣት አራዓያ የሚሆን ነው ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
በሳህሉ ብርሃኑ