በግምገማችን አዲስ አበባን ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ውብ፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ አበረታች ውጤቶችን አይተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing በግምገማችን አዲስ አበባን ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ውብ፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ አበረታች ውጤቶችን አይተናል – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN ጥር 18/2018 ዓ.ም

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸዉ ባሰፈሩት መልዕክት “በትጋት አዲስ አበባን ወደ ላቀ ስኬት!” በሚል መሪ ሃሳብ ባለፉት ቀናት ስናካሂድ የነበረዉን የከተማችንን የ2018 በጀት ዓመት የ6 ወራት የመንግስትና የፓርቲ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ በስኬት አጠናቀናል ብለዋል፡፡

በግምገማችንም አዲስ አበባን ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ውብ፤ ለነዋሪዎቿ ምቹ እና ዘመናዊ ከተማ ለማድረግ የተከናወኑ አበረታች ውጤቶችን አይተናል። ለአብነትም 134 ኪ.ሜ አዳዲስ መንገዶች የተገነቡ ሲሆን፣ ከ573 ኪ.ሜ በላይ መንገዶችም ጥገና ተደርጎላቸዋል።

በውሃና ፍሳሽ፦ የውሃ አቅርቦትን በ60 ሺህ ሜትር ኩብ ለማሳደግ ውጤታማ ስራ ተሰርቷል። የፍሳሽ ማስወገጃ ስርዓቱን በማዘመን ከተማችንን ከብክለት ለመከላከል የ8 ማጣሪያዎች ግንባታ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ይገኛል ብለዋል፡፡

ለህዝባችን ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት በትምህርት፣ በጤና እና በተለያዩ ማህበራዊ ዘርፎች የህዝቡን አዳጊ ፍላጎት መሰረት ያደረጉ 274 ፕሮጀክቶች ግንባታ ላይ ናቸው። በኮሪደር ልማትና በወንዝ ዳርቻ ስራዎችም ከተማችንን መልሰን እየገነባን፣ ከከተማችን አልፈን የሀገራችንን ገጽታ ቀይረናል። ለነዋሪዎቻችን 12 ሺህ የመኖሪያ እና የንግድ ቤቶችንም ገንብተን ለተጠቃሚዎች አስተላልፈናል።

የከተማችን የኮንፍረስ ቱሪዝም መዳረሻነት በከፍተኛ ሁኔታ ያደገ ሲሆን ባለፉት 6 ወራት ከ150 በላይ ኮንፍረንሶች ተካሂደዋል። በስራ ዕድል ፈጠራ ከ195 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ እና ለበርካቶች በጊዜያዊነት የስራ ዕድል የመፍጠር ስራ ተከናዉኗል።

ከህዝቡ ቅሬታ ከሚቀርብበት የአገልግሎት አሰጣጥ አንፃርም በ’መሶብ’ የአገልግሎት አሰጣጥ የ94 % የህዝብ እርካታ ማግኘት መጀመራችን ለቀጣይ ስራችን ትልቅ ስንቅ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡

የበጎ ፈቃድ ተሳትፎም በከፍተኛ ሁኔታ በማደግ ከባለድርሻ የልማት አጋሮቻችን እና ከሕዝባችን 13 ቢሊዮን ብር የሚገመት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በማበርከት ከፍተኛ የሕዝብ አጋርነት የታየበትም ነበር።

በቀጣዮቹ 6 ወራትም ትኩረት የሚሹ የአመራር አፈፃፀም ልዩነቶችን በማጥበብ፣ ተቋማዊ ግንባታን ለማጠናከር፣ ጉበኝነትና ብልሹ አሰራርን በዘመናዊ አሰራር እና በህዝባችን ተሳትፎ ለማምከን፣ የመረጃ አያያዝን ለማዘመን እንዲሁም የኑሮ ውድነትን ጫና ለመቀነስ የተጀመሩ ስራዎችን ለመቀጠል የገቢ አሰባሰብን አጠናክረን ለመስራት የተግባባንበት ውጤታማ መድረክ ነበር ሲሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ መልእክት አስተላልፈዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review