AMN ጥር 20/2018 ዓ.ም
አሜሪካ የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ትብብርን ለማሳደግ ቁርጠኛ መሆኗን የአሜሪካዉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ክሪስቶፈር ላንዳው ገለጹ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ከአሜሪካዉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሚስተር ክሪስቶፈር ላንዳው ጋር ውይይት አድርገዋል።
በዉይይቱ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዢ ኢዮብ ተካልኝ(ዶ/ር) የተገኙ ሲሆን በኢትዮጵያ ማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም፣ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን በማስፋፋት እና በሁለቱ አገራት መካከል እያደገ በመጣው አጋርነት ዙሪያ ዉይይት አካሂደዋል፡፡
አቶ አህመድ ሽዴ በዉይይቱ የኢትዮጵያ የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አፈጻጸምን በተመለከተ በተለይ በተመዘገቡ አዎንታዊ ውጤቶችና እየተሻሻለ በመጣው የሃገሪቱ ኢኮኖሚ ዙሪያ ማብራሪያ ሰጥተዋል።
የኢኮኖሚ ሪፎርም ማሻሻያዎቹ የኢንቨስትመንት ምህዳሩን በከፍተኛ ሁኔታ ማሻሻላቸውንና በዋና ዋና የኢኮኖሚ ዘርፎች የተሻለና ተወዳዳሪ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን መፍጠር መቻሉን ሚኒስትሩ አጽንኦት ሰጥተው ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ በኢትዮጵያ እና በአሜሪካ መካከል ያለውን ጠንካራ እና እያደገ የመጣ የሁለትዮሽ አጋርነት ያነሱ ሲሆን፤ የዩናይትድ ስቴትስ መንግስት በኢትዮጵያ የጤናዉን ዘርፍ ለመደገፍ ላሳየው የቅርብ ጊዜ ቁርጠኝነት አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም ዩናይትድ ስቴትስ በባለብዙ ወገን የፋይናንስ ተቋማት በኩል ለኢትዮጵያ አጠቃላይ የልማት ጥረቶች እያደረገች ያለውን ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እውቅና ሰጥተዋል።
ሚኒስትሩ ለምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ስለ ኢትዮጵያ ግዙፍ የአዲሱ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ፕሮጀክት ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ፕሮጀክቱ ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ ለቀጠናዊ ትስስር እና ለንግድ ማሳለጫ ያለውን ስልታዊ ጠቀሜታ ገልጸዋል።
የአሜሪካዉ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው በኢትዮጵያ መንግስት በማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም በኩል የተመዘገበውን አጠቃላይ መሻሻል አድንቀዋል።
አሜሪካ የንግድ ተሳትፎ እና ኢንቨስትመንት በኢትዮጵያ እንዲሰፋ ያላቸውን ከፍተኛ ፍላጎት የገለጹ ሲሆን፣ የሁለትዮሽ ትብብሩን የበለጠ ለማጠናከር ያላቸውን ቁርጠኝነት በድጋሚ አረጋግጠዋል።
ሁለቱም ወገኖች የኢትዮጵያ- እና አሜሪካን አጋርነትን ለማጠናከር ፣ የግል ዘርፉን ተሳትፎ ለማሳደግ እና የኢትዮጵያን ዘላቂ የኢኮኖሚ ልማት ለመደገፍ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ትብብርን ለማሳደግ ያላቸውን የጋራ ቁርጠኝነት መግለጻቸዉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡