AMN – ሐምሌ 9/2018 ዓ.ም
ኢትዮጵያ ለዘመናት የዘለቁ ውስብስብ ልዩነቶቿን በጠረጴዛ ዙሪያ ለመፍታት የሚያስችላትን ታሪካዊ የሆነውን ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ በትላንትናው ዕለት በይፋ ጀምራለች።
ይህ መድረክ በሀገሪቱ ስር የሰደዱ ችግሮች ከስረ መሰረታቸው ለመፍታት ያለመ በመሆኑ በታሪክ ውስጥ አዲስ ምዕራፍ ይከፍታል ተብሎ ይጠበቃል።
ጉባዔው ለዘመናት መፍትሄ ያላገኙ መሰረታዊ ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ትልቅ በር ይከፍታል።
በተለይም የሀገር ግንባታ፣ የማንነት እና የሀገር ባለቤትነት ጉዳዮች፣ ታሪክ እና ማንነት፣ የጋራ ሀገራዊ ማንነት እና እሴቶች፣ ሀገር ግንባታና ብዝሀነት፣ የቋንቋ፣ የባሕል፣ የታሪክና ቅርስ ጥበቃ የጉባኤ ተሳታፊዎች በቀዳሚነት የሚመክሩባቸው ጭብጦች ናቸው።

የመንግሥት አደረጃጀትና ቅርጽ፣ የፖለቲካ ሥርዐትና የፖለቲካ ውክልና እንዲሁም የምርጫ ሥርዐት በሁለተኛ ደረጃ የተቀመጡ የውይይት ርእሶች ናቸው፡፡
በነዚህ በተመረጡ አጀንዳዎች ላይ ያሉ ልዩነቶችን በማቀራረብ ረገድ የምክክር ጉባዔው የሚኖረው ፋይዳ የጎላ ነው።
ከዚህም በላይ ዜጎች በነፃነት የሚወያዩበትን የዲሞክራሲ ባህል በማሳደግ አስተማማኝ መረጋጋትን ለመፍጠር እና የሀገርን ምርታማነት በማሳደግ ለኢኮኖሚ ትንሳኤ ዋነኛ ምሰሶ እንደሚሆን ይታመናል።
የዚህን ታሪካዊ ዕድል ስኬታማነት ለማረጋገጥ፣ መንግስት የምክክር ኮሚሽኑ ያለምንም ጣልቃ ገብነት በነፃነትና በገለልተኝነት እንዲሰራ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ ትልቅ አቅም መሆኑን የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ በትላንትናው ዕለት በጉባዔው መክፈቻ ላይ ገልጸዋል።

የጉባዔው ተሳታፊዎች የምክክሩ ዋና ባለቤት መሆናቸውን ተረድተው፣ ልዩነቶቻቸውን በጥላቻ ሳይሆን በውይይትና በመደማመጥ መፍታት ይኖርባቸዋል።
በዚህ ታሪካዊ መድረክ ላይ ከጠባብ የቡድን ጥቅም ይልቅ የሀገርን የጋራ ህልውና ማስቀደም የዜግነት ግዴታቸው ሊሆን ይገባል።
ይህ ሀገራዊ ምክክር ጉባዔ ኢትዮጵያን ወደ ብሩህ ተስፋ የሚወስድ ብቸኛ ድልድይ በመሆኑ፣ እያንዳንዱ የጉባዔው ተሣታፊ በኃላፊነት ስሜት የነገዋን አዲስ ኢትዮጵያ ለመገንባት የሚያስችል መሠረት ለመጣል የድርሻውን በመወጣት የጉባዔውን ስኬት ማረጋገጥ ይኖርበታል።