AMN- ጥር 24/2018 ዓ. ም
የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን በሃገሪቱ የመጀመሪያ የሆነውን በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ ያስገነባው ዘመናዊ የማቀዝቀዣ መጋዘን (Cold Store)፣ አምራችና ሸማችን በቀጥታ በማገናኘት በዘርፉ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል።
ይህ ዘመናዊ መሠረተ ልማት በዋናነት የተገነባው ከአዝመራ ሰብሰባ በኋላ የሚከሰተውን ከፍተኛ የምርት ብክነት ለመቀነስና በአምራችና በሸማች መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት በመፍጠር የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር መሆኑ ተገልጿል።
የማዕከሉ አስተባባሪ አቶ ዘላለም ግርማ እንደገለጹት፣ መጋዘኑ ምርቶችን በጥራት በማቆየት ለተጠቃሚው በአግባቡ ለማድረስና ብክነትን ለመከላከል ትልቅ ፋይዳ አለው።
በሀገራችን በርካታ የግብርና ምርቶች ገበያ ላይ ሳይውሉ የሚበላሹበትን አሳዛኝ ሁኔታ ለመቀየር ይህ ማዕከል ቁልፍ ሚና ይጫወታል ብለዋል።

ማዕከሉ ምርቶችን እንደ ባህሪያቸው ለይቶ የሚያቆዩ የተለያዩ ክፍሎች ያሉት ሲሆን፣ በተለይም ፈጣን ማቀዝቀዣ (Fast Cooling) የሚፈልጉ እንደ ቲማቲምና እና ጎመን ዝርያዎች እንዲሁም የፍራፍሬ ምርቶችን ትኩስነታቸው ሳይቀየር ለረጅም ጊዜ ለማቆየት ያስችላል።
እንዲሁም ብርቱካንና ሀባብ በራሳቸው የሚያመነጩት ጋዝ (Ethylene) ሌላውን ምርት እንዳያበላሽ ተለይተው እንዲቀመጡ ይደረጋል።
የወተት ተዋጽኦዎችና እንደ እንጆሪ ያሉ ስስ ምርቶች ጥራታቸውን ሳይለቁ እንዲቆዩ በከፍተኛ ቅዝቃዜ ( ከዜሮ ዲግሪ በታች ባለው ቅዝቃዜ) ውስጥ ይቀመጣሉ።
የማዕከሉ የጥራት ተቆጣጣሪ አቶ ሳለጌታ በላይ እንደገለጹት፣ በማቀዝቀዣው ውስጥ የቆዩ ምርቶች ከሁለት ሳምንት በኋላም ቢሆን ልክ ከዛፍ እንደወረዱ ትኩስ ሆነው ለገበያ ይቀርባሉ።

ይህ ማዕከል ለ12 ወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ማህበረሰቡ ምርቶችን በተመጣጣኝ ዋጋ እንዲያገኝ ረድቷል።
የኢትዮጵያ ንግድ ስራዎች ኮርፖሬሽን ይህንን ማዕከል እንደ አንድ የንግድ ማዕከል በመጠቀም የአርሶ አደሩን ምርቶች ጥራታቸውን በጠበቀ መልኩ ለዓለም አቀፍ ገበያ ለማቅረብ አቅዷል።
ይህ ሂደት የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከማሳደጉም በላይ የኢትዮጵያን የግብርና ምርቶች በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ ያደርጋል ሲሉ አቶ ዘላለም ተናግረዋል።
የቃሊቲ የተገነባው ይህ ዘመናዊ መጋዘን በኢትዮጵያ የግብርና ምርት ሰንሰለት ውስጥ የሚታየውን የጥራትና የብክነት እንዲሁም ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ ችግርን ለመፍታት የተወሰደ ተጨባጭ እርምጃ ነው መሆኑን አስተባባሪው ገልፀዋል።
በቶለሳ መብራቴ