AMN-ጥር 27/2018 ዓ.ም
ተቋሙ የተሽከርካሪዎች ሰሌዳ መቀየርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ተሰጥቷል ።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ ለ50 ዓመታት ያክል ሲጠቀምበት የቆየውን የተሽከርካሪ ታርጋ ለውጥ ማድረጉን አስታውቋል ።
ይሕንንም በማስመልከት ተቋሙ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አዲሱ የተሽከርካሪ ታርጋ ከዚሕ ቀደም የነበረውን ወጥነት የጎደለው የሰሌዳ ስርዓትን በማስቀረት በምትኩ ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የታርጋ ስርዓት እንዲኖር የሚያስችል መሆኑ ተጠቅሷል።
ከዚህ ቀደም የነበረው የተሽከርካሪ ታርጋ ቀለምና ቁጥርን ብቻ የያዘ በመሆኑ በቀላሉ ለፎርጅድ አሰራር የተጋለጠ መሆኑን የፌደራል ፖሊስ የሎጂስቲክ መምሪያ ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር እሸቱ ፊጣ ተናግረዋል።

አዲሱ ታርጋ የተቋሙ ሎጎን የያዘ እንዲሁም ሚስጥራዊ መለያ ያላቸው ባር ኮዶችን ያካተተ በመሆኑ ተቋሙ የሚሰጠውን አገልግሎት ፈጣን ግልፅና ተጠያቂነት ያለው ለማድረግ እንደሚያስችልም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተመላክቷል።
የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ 2030 እንደሀገር የተያዘዉን የዲጅታል ኢትዮጵያዊ ልማት ለማሳካት በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ ሲሆን ይሕም አንዱ የዲጂታላይዜሽን ልማት አካል መሆኑ ተገልጿል።
በአይነቱ የመጀመሪያ የሆነው አዲሱ የተሽከርካሪ ታርጋ ጥር 28/2018 ዓ.ም በይፋ ስራ ላይ የሚውል መሆኑ በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተገልጿል።
በታምሩ ደምሴ