AMN — የካቲት 04/2018 ዓ.ም
የአፍሪካ ሕብረት ጉባኤ በአዲስ አበባ መካሄዱ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ትልቅ የዲፕሎማሲ ዕድል መሆኑን የፖለቲካ ምሁር የሆኑት ሰለሞን ተፈራ ገልጸዋል፡፡
39ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ የካቲት 7 እና 8/2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል፡፡
ከአዲስ ሚዲያ ኔትዎርክ ጋር ቆይታ ያደረጉት የፖለቲካ ምሁሩ ሰለሞን ተፈራ እንደገለጹት፣ የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄዱ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች እንዳለው አብራርተዋል፡፡
መሪዎቹ ከዋናው ጉባኤ ጎን ለጎን የሚያደርጓቸው የሁለትዮሽና የባለብዙ ወገን ውይይቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ለማስተዋወቅና በአፍሪካ ቀንድ ያላትን ሚና ለማሳወቅ ምቹ አጋጣሚ እንደሚፈጥር ምሁሩ ገልጸዋል።

አዲስ አበባን የቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የተሰሩ የልማት ስራዎች ለመሪዎች የሚታዩበት ዕድል መፈጠሩ የሀገሪቱን ገጽታ ከመገንባቱም ባለፈ፣ መሪዎች ሌሎች ጎብኚዎችን እንዲጋብዙ በማድረግ ለኢኮኖሚው ዕድገት የራሱን ድርሻ ያበረክታል ብለዋል።
ኢትዮጵያ በትግራይ የነበረውን ግጭት በሕብረቱ ጥላ ስር እንዲፈታ በማድረግና በታላቁ የሕዳሴ ግድብ ጉዳይ የያዘችው አቋም “አፍሪካዊ መፍትሔ ለአፍሪካ ችግሮች” ለሚለው መርህ ትልቅ ማሳያ መሆኑ የገለጹት ምሁሩ፣ አፍሪካውያን ከባዕድ አጀንዳዎች ይልቅ የራሳቸውን ሰላም የማረጋገጥ ባህል ሊያዳብሩ እንደሚገባም አሳስበዋል።
በአፍሪካ ቀንድ ከውኃ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ጉዳዮች ዓለም አቀፍ ሕጎችን ተከትለውና በሕብረቱ ማዕቀፍ እንዲፈቱ ማድረግ፣ አፍሪካ በ2063 ለማሳካት ላቀደችው የብልጽግና ግብ ወሳኝ መሆኑን ምሁሩ አብራርተዋል።
54ቱም የአባል ሀገራት የፓን አፍሪካኒዝምን ጽንሰ-ሐሳብ በመረዳትና ራሳቸውን በማስከበር የሕብረቱን ዓላማ ለማሳካት የበኩላቸውን ሚና መወጣት እንዳለባቸው ሰለሞን ተፈራ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
በአስማረ መኮንን