AMN- የካቲት 6/2018 ዓ.ም
የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነትን (CFA) ያጸደቁ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች፣ የዓባይ ውሃን በፍትሐዊነት እና በምክንያታዊነት ለመጠቀም ያላቸውን ጽኑ አቋም በድጋሚ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌድዮን ጢሞቴዎስ (ዶ/ር)፣ የስምምነቱ አባል ከሆኑት የኬንያ፣ የሩዋንዳ፣ የታንዛኒያ፣ የኡጋንዳ፣ የብሩንዲ እና የደቡብ ሱዳን አቻዎቻቸው ጋር ዛሬ በአዲስ አበባ ውጤታማ ውይይት አካሂደዋል።
ስምምነቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ለማስገባት እና የዓባይ ወንዝ ተፋሰስ ኮሚሽንን (NRBC) በአስቸኳይ ለማቋቋም በሚያስችሉ ተግባራዊ እርምጃዎች ላይ መክረዋል።
ሚኒስትሮቹ የዓባይ ተፋሰስ የትብብር ማዕቀፍ ስምምነት ውስጥ የተካተቱትን የፍትሐዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርሆዎች በጋራ ለማስፈጸም ያላቸውን ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል።
የጋራ የውሃ ሀብት የሆነውን የዓባይ ወንዝን በውጤታማነት ለማስተዳደርና ለመጠቀም የሁሉም ተፋሰስ ሀገራት ትብብር አስፈላጊነት ላይ ተስማምተዋል።
ስምምነቱ በሥራ ላይ ከዋለበት ጊዜ ጀምሮ የተመዘገቡ ስኬቶች የተገመገሙ ሲሆን፣ የቀሩ የተቋማዊ ግንባታ ሥራዎችን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጧል።
ሚኒስትሮቹ በውይይቱ ማጠቃለያ ላይ፣ የዓባይ ተፋሰስ ሀገራት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ትብብር እንዲያደርጉ ጥሪ መቅረቡን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያገኘነው መርጃ ያመለክታል።