• ከተማን ለሰው ልጆች ምቹ ከማድረግ አንጻር አዲስ አበባ እያከናወነች ያለው ተግባር የሚደነቅ መሆኑ ተጠቁሟል
ባለፉት ጥቂት ዓመታት አዲስ አበባ የምስራቅ አፍሪካ የንግድ እና የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን ብቻ ሳይሆን፣ አህጉራዊ የከተማ ልማት ፋና ወጊነቷን በተግባር እያስመሰከረች ትገኛለች። ከተማዋ እያከናወነችው ያለው ግዙፍ የኮሪደር ልማት፣ የፓርኮች ግንባታ እና የወንዞች ዳርቻ ማሻሻያ ፕሮጀክቶች በዓለም አቀፍ ተቋማት እና በጎረቤት ሀገራት ዘንድ እንደ “ተአምራዊ ሽግግር” ተቆጥሯል። ዛሬ አዲስ አበባን የሚጎበኙ አፍሪካውያን መሪዎች፣ የዓለም አቀፍ ተቋማት ኃላፊዎና ተወካዮች፣ የከተማ ፕላን ባለሙያዎች እና ሌሎች እንግዶች በአዲስ አበባ የሚኖራቸውን ቆይታ አጠናቅቀው የሚመለሱት በቃላት የሚገለጽ አድናቆትን በማቅረብ ብቻ አይደለም፤ ለሀገራቸው እና ከተሞቻቸው የሚሆን አዲስ የልማት ርዕይንም ሰንቀው ነው።
በቅርቡ፣ ማለትም በወርሃ ጥር አጋማሽ 2018 ዓ.ም. ላይ በአፍሪካዊያኑ መዲና፣ አዲስ አበባ አንድ ሁነት ተከናውኗል። ይህ ሁነት የተለያዩ የአፍሪካ ከተሞች ከንቲባዎች እና የክልል አስተዳዳሪዎች የተሳተፉበት የመማማሪያ መድረክ ነው፡፡ የሁነቱ መነሻ ምክንያት ከአዲስ አበባ ዘርፈ ብዙ ስኬት የሚመነጭ ነው፡፡ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) አማካኝነት በአፍሪካ ከተሞች የፋይናንስ አስተዳደር (Financial Management) አፈፃፀም ላይ በተካሄደው ጥልቅ የዳሰሳ ጥናት መሠረት፤ አዲስ አበባ ከተማ ከተመዘነችባቸው 6 መስፈርቶች ውስጥ በ5ቱ የላቀ አፈፃፀም በማስመዝገቧ እና የስኬቷን ልምዷን እንድታካፍል በመመረጧ ነው፡፡
ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ እንደሚያመላክተው፤ ጥናቱ አዲስ አበባን ጨምሮ በስድስት የአፍሪካ ሀገራት ከተሞች ላይ ተካሂዷል። እነዚህ ከተሞች፡- የኬንያዋ ናይሮቢ፣ የታንዛኒያዋ ዳሬሰላም፣ የዛምቢያዋ ሉሳካ፣ የሩዋንዳዋ ኪጋሊ እና የካሜሮኗ ያውንዴ ናቸው፡፡ ከከተሞቹ መካከል አዲስ አበባ የተሻለ አፈፃፀም በማስመዝገብ ቀዳሚ መሆን ችላለች። በተለይም የገቢ እና የፋይናንስ ሀብት አስተዳደርን በማዘመን ረገድ የጀመረችው ሪፎርም ውጤታማና ለአፍሪካ ከተሞች አርአያ መሆኑን የጥናቱ ግኝት አረጋግጧል።
የአዲስ አበባን ስኬታማ ተሞክሮ ያካፈሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤም፤ በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ኢኮኖሚ ኮሚሽን (UNECA) አማካኝነት በአፍሪካ ከተሞች የፋይናንስ አስተዳደር (Financial Management) አፈፃፀም ላይ የተደረገው የጥናት ውጤት የሚያረጋግጠው የአዲስ አበባን ስኬታማነት መሆኑን ገልፀዋል። “ይህ ስኬት፤ ከተማችን ከምትሰበስበው አጠቃላይ ገቢ ውስጥ 71 በመቶውን ለልማት ሥራዎች በመመደብ፣ የዜጎችን ዘላቂ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ስናደርግ የቆየነው የሪፎርም ጉዞ ውጤታማነት ማሳያ ነው፡፡ ከተለያዩ ከተሞች ለልምድ ልውውጥ የመጡት ተሳታፊ ከንቲባዎች እነዚህን የሪፎርም ሥራዎች በአካል በመጎብኘት፣ አዲስ አበባ በፋይናንስ እና በገቢዎች ሥራ አቅሟን እንዴት ገንብታ ወደ ተግባራዊ ለውጥ እንደቀየረችው ሰፊ ተሞክሮ አጋርታለች” ብለዋል፡፡ መድረኩ የአፍሪካ ከተሞች የወደፊት ዕጣ ፈንታ በጋራ የሚቀረጽበት ታሪካዊ አጋጣሚ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአፍሪካዊያን እና በሌሎች የዓለም ሀገራት ላይ የከተማ ልማት ተምሳሌት ተደርጋ እየተወሰደች ያለችው አዲስ አበባ፤ የጁባ እና ናይሮቢ ከተሞች ከፍተኛ አመራሮችንና ልዑካንን በስኬታማ ሥራዋ ስባ ማምጣቷን በአብነትነት መጥቀስ እንችላለን፡፡ ለጉብኝታው መነሻው፣ ከ2010 ዓ.ም. በኋላ በከተማዋ ተዓምራዊ ለውጥ እያመጣ ያለው የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻ ልማት፣ የትላልቅ ፕሮጀክቶች ግንባታ እና ተያያዥ ውጤታማ ሥራዎች ናቸው፡፡ የደቡብ ሱዳን ከፍተኛ የልዑካን ቡድን አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት፣ ዋና ከተማቸው ጁባን ለማዘመን የአዲስ አበባን የኮሪደር ልማት እንደ ዋና መመሪያ ለመጠቀም መወሰናቸውን ገልጸዋል። የደቡብ ሱዳን አመራሮች በተለይ የተደነቁት በህንፃዎቹ ውበት ብቻ ሳይሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሰፊ ስራን የመጨረስ የአመራር ጥበብን ነው። “ይህ ለአፍሪካ ከተሞች አዲስ ተስፋ ነው” በማለት ምስክርነታቸውን የሰጡት እነዚህ አመራሮች፣ ኢትዮጵያ የራሷን የውስጥ አቅም ተጠቅማ እንዲህ ያሉ ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መፈጸሟ ለጁባ እድገት ትልቅ ትምህርት መሆኑን ማረጋገጣቸው ይታወሳል፡፡
በተመሳሳይ፣ የናይሮቢው ገዢ ጆንሰን ሳካጃ አዲስ አበባን በጎበኙበት ወቅት በሰጡት አስተያየት፣ አዲስ አበባ “ከተማን ለሰው ልጆች ምቹ ማድረግ” የሚለውን መርህ በተግባር ያሳየችበት መንገድ አድንቀዋል። ናይሮቢ አሁን ላይ የጀመረችውን የኡሁሩ ፓርክ እድሳት እና የናይሮቢ ወንዝን የማጽዳት ፕሮጀክት ከአዲስ አበባው የ“ገበታ ለሸገር” እና የፓርኮች ልማት ጋር የተቆራኘ መሆኑን የኬንያ ሚዲያዎች በዘገባዎቻቸው በስፋት እየመሰከሩ ይገኛሉ።
የዓለም ባንክ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች የአዲስ አበባን በዓይን የሚታይ፣ በእጅ የሚዳሰስ፣ በአፍንጫ የሚሸተት፣ “ሠው ተኮር” የልማት ፕሮጀክት ውጤትን በቸልታ የሚያልፉት አልሆነም። ይልቁንም፤ ለአዲስ አበባ ውጤታማ ሥራ ዕውቅና ከመስጠት ባሻገር ሌሎች እንዲማሩበት ልምድ የሚቀምሩባት የልማት አውድማ ሆናቸዋለች፡፡ ለዚህም ነው፤ የዓለም ባንክ አዲስ አበባን “ፈጣን ሽግግር እያደረገች ያለች ከተማ” በማለት የሚገልጻት። በተፈጥሮ ሃብትና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን ያደረገው “ዩኤን-ሃቢታት (UN-Habitat)” የተሰኘው ዓለም አቀፍ ተቋም በበኩሉ፤ የአዲስ አበባን የወንዝ ዳርቻ ልማት ለአካባቢ ጥበቃ እና ለከተማ ኑሮ ጥራት እንደ “ምርጥ ተሞክሮ” (Best Practice) ወስዶ ለሌሎች የአፍሪካ አገራት በማስተዋወቅ ላይ ይገኛል።
የከተማ ልማት አፍሪካዊት ፈርጥ ተደርጋ እየተወሰደች ስላለችው አዲስ አበባ፣ በምሁራዊ ዕይታ ተመልክተው የውጤታማነት ምስጢሩ ምን እንደሆነ እንዲያስረዱን፣ በኢትዮጵያ ፐብሊክ ሰርቪስ ዩኒቨርሲቲ የከተማ ልማትና ጥናት ኮሌጅ ምክትል ዲንና መምህር ሄርጶ በሪሶን (ዶ/ር) አነጋግረናቸዋል። እሳቸውም፤ “ይህ ዘመን የከተሜነት ዘመን ነው፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ ከተሞች በጣም እየተስፋፉ ነው፡፡ የሠዎች የመኖሪያ መዳረሻ ከተሞች እየሆኑ ነው። በበለፀጉት ሀገራት በከተሞች የሚኖረው ሕዝብ 90 ከመቶ ደርሷል። አፍሪካ እንደ አህጉር የከተማ ነዋሪው ሕዝብ ቁጥር 40 ከመቶ አካባቢ ሆኗል፡፡ በኢትዮጵያ ያለው ድርሻ 25 ከመቶ አካባቢ ነው” በማለት ስለ ከተማና ከተሜነት አሁናዊ ሁኔታ አጭር መግለጫ በመስጠት ማብራሪያቸውን ጀምረዋል፡፡
አክለው እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ መንግስት ዘመኑን የተረዳ የመሆኑ ማሳያው በአዲስ አበባ እየተከናወነ ያለው ሁሉን አቀፍ የከተማ ልማት ሥራ ነው። ልማቱን ከሌላው ለየት የሚያደርገው፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሠፊ እና ግዙፍ ሥራ መሠራቱ ነው። በዚህም ተጨባጭ ውጤት ማምጣት ችሏል፡፡
“በአዲስ አበባ የተከናወነውና እየተከናወነ ያለው ልማት ሠው ተኮር ነው፡፡ ሁሉንም የሕብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ የሚያደርግ ነው፡፡ መሰረተ ልማቶችን አስፋፍቷል፤ አዘምኗል፡፡ የሕዝብ መዝናኛ እና ማረፊያ ሥፍራዎችን አበራክቷል፡፡ የአረንጓዴ ልማት ሽፋንን አሳድጓል፡፡ ወንዞችና የወንዝ ዳርቻዎች ከአደጋ የሚጠበቁበትን ሁኔታ ፈጥሯል፡፡ ይህ ደግሞ ከተማዋ ለነዋሪዎቿ ምቹ፣ ፅዱ እና ውብ እንድትሆን ትልቅ ሚና ይጫወታል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሄርጶ በሪሶ (ዶ/ር)፤ ከተሜነት ከሚገለጽባቸው መመዘኛዎች መካከል፡- የአገልግሎት አሠጣጥ መዘመንና መሻሻል ሌላኛው ነው፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመንግስት አገልግሎትን በዲጂታል ቴክኖሎጂ እንዲታገዝ የማድረጉ ጅምር በጣም የሚበረታታ ነው፡፡ በተለይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በተሠራ ጥናት ከሌሎች የአፍሪካ ሀገራት ተሽላ እንድትገኝ፣ ተሞክሮዋንም ለሌሎች እንድታካፍል ያደረጋት ዘመናዊና በቴክኖሎጂ የተደገፈ የፋይናንስ አስተዳደሯ በማሳያነት የሚጠቀስ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
“አዲስ አበባ ከተማ እያሳየች ባለችው ውጤታማ የልማት እንቅስቃሴ የብዙዎችን ቀልብ እየሳበች ነው። የአፍሪካ ከተሞች የልማት ሞዴል ተደርጋም እየቀረበች ነው። አድናቆቱ ሊመጣ የቻለው በአዲስ አበባ የከተማ ልማት ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ግዙፍ ልማት መከናወኑና ለውጥ መምጣቱ ነው፡፡ ይህ ዓለም አቀፍ ምስክርነት አዲስ አበባን በይበልጥ ለማስተዋወቅ፣ የከተማዋን ልማትና የቱሪዝም ተጠቃሚነት ለማሳደግ ትልቅ አቅም ይፈጥራል” በማለት የገለፁት ሄርጶ (ዶ/ር)፤ በከተማዋ እየታየ ያለውን የልማት ለውጥ ለማስቀጠልና ዘላቂ ለማድረግ መሠራት ይገባቸዋል ያሏቸውን ምክረ ሃሳቦች አመላክተዋል። የተሠሩ፣ እየተሠሩ ያሉና በቀጣይነት የሚሠሩ የልማት ፕሮጀክቶች በጣም ሰፊና ግዙፍ ናቸው፡፡ እነዚህን የልማት ሥራዎች የሚያስተዳደር፣ የሚከታተል፣ ጥገናና ማሻሻያ የሚያደርግ ጠንካራ ተቋማዊ አቅም መገንባት ያስፈልጋል። በተቻለ መጠን የልማት ሥራውን አካታችነት የበለጠ ማጠናከር ይገባል፡፡ በልማቱ ላይ የሕዝብ፣ የግል ተቋማትን፣ የባለሃብቶችን… ተሳትፎ ማሳደግ እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡
በደረጀ ታደሰ