ልጆች፤ ስለ አፍሪካ ህብረት ምን ያህልታውቃላችሁ?

You are currently viewing ልጆች፤ ስለ አፍሪካ ህብረት ምን ያህልታውቃላችሁ?

በፋንታነሽ ተፈራ

ልጆች፤ አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻም ሳይሆን የአፍሪካ መዲና መሆኗን ታውቃላችሁ? በዛሬው ጽሑፋችን ከተለያዩ የመረጃ ምንጮች አደራጅተን ስለ አፍሪካ ህብረት አመሰራረት፣ አዲስ አበባ ለ39ኛ ጊዜ እያስተናገደችው ስላለው የህብረቱ ጉባኤ እና ስላደረገችው ዝግጅት በጥቂቱ ይዘንላችሁ ቀርበናል፤ መልካም ንባብ፡፡

ልጆች የአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ሀገራት ተስማምተው የመሰረቱት ድርጅት ነው፡፡ ድርጅቱም ኢትዮጵያን ጨምሮ 55 አባል ሀገራት አሉት።

የዛሬው የአፍሪካ ህብረት የቀድሞው መጠሪያው “የአፍሪካ አንድነት ድርጅት” በሚል ነበር፡፡ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት መቀመጫውን በኢትዮጵያ ዋና ከተማ በአዲስ አበባ አድርጎ በ32 የአፍሪካ ሀገራት ግንቦት ወር 1955 ዓ.ም ተመሰረተ፡፡

ልጆች፤ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት የራሱ ዓላማዎች ነበሩት። ይኸውም ቅኝ ገዢዎችን ማስወገድ፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል አንድነትና ህብረትን ማበረታታት፣ ለአፍሪካውያን የተሻለ ህይወት እና እድገት ማምጣት፣ ነፃነትን ማስጠበቅ፣ ሰብአዊ መብቶችን ማስከበር፣ በአፍሪካ ሀገራት መካከል የሚካሄዱትን ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ መፍታት የሚሉ ነበሩ።

የአፍሪካ አንድነት ድርጅት እ.ኤ.አ. በ2002 “የአፍሪካ ህብረት” የሚል መጠሪያ አገኘ፡፡ ህብረቱ ራዕይ ነበረው። ራዕዩም የተቀናጀች፣ የበለጸገች እና ሰላማዊ፣ በራሷ ዜጎች የምትመራ እና በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ተፎካካሪ የሆነች አፍሪካን መመስረት ነው።

ልጆች፤ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የአሁኑን የአፍሪካ ህብረት በመመስረት ቁልፍ ሚናን የተጫወቱ የአፍሪካ አባቶች 32 ናቸው፡፡ ከነዚህም አባቶች መካከል የኢትዮጵያ ንጉሠ ነገሥት ቀዳማዊ ኃይለ ስላሴ፣ የጋናው መሪ ክዋሜ ንክሩማህ፣ የኬንያው መሪ ጆሞ ኬንያታ፣ የሴኔጋል የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሴዳር ሴንጎር፣ የታንዛኒያ ፀረ-ቅኝ ግዛት ታጋይ፣ ፖለቲከኛ እና የፖለቲካ አቀንቃኙ ጁልየስ ኔሬሬ እና ሌሎችም ይጠቀሳሉ፡፡

ልጆች፤ የዘንድሮው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ በዋና መሥሪያ ቤት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡ አዲስ አበባም በአኩሪ የእንግዳ አቀባበል ባህሏ ተቀብላቸዋለች፡፡ ይህን እያደረገች ያለው ኮሪደሩ እና የወንዝ ዳር ልማቱ በፈጠሩላት ውበትና ጽዳት መሆኑ ለከተማዋ እና ለሀገር ፋይዳው ብዙ ነው፡፡ ይህ ደግሞ በከተማችን ብሎም በሀገራችን እንድንኮራ ያደርገናል፤ አይደል ልጆች? በዚህ ላይ ከጓደኞቻችሁ ጋር ሀሳብ ተለዋወጡ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review