በመዲናችን አዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች እና አዳዲስ ጥበባዊ ሥራዎች ለጥበብ አፍቃሪያን ሲደርሱ ቆይተዋል፡፡ ዛሬን ጨምሮ በሚቀጥሉት ቀናትም የተለያዩ ጥበባዊ መሰናዶዎች ይደረጋሉ፡፡ ከተሰናዱ ዋና ዋና ኪነ ጥበባዊ ዝግጅቶች መካከል የሐሳብ እና ንባብ ውይይት፣ የሥዕል አውደ ርዕይ፣ የመጽሐፍት ምረቃ፣ የቴአትር መርሃ ግብር እና ሌሎች መሰናዶዎች ይገኙበታል፡፡ ለመረጃ ይሆንዎት ዘንድ የአዲስ ልሳን ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል እንደሚከተለው አዘጋጅቷቸዋል፡፡
መጽሐፍት
“እንዲህም ተኑሯል” መጽሐፍ በዛሬው ዕለት ይመረቃል፡፡ ከ21 በላይ መጻሕፍትን ለንባብ ያበቃው ጋዜጠኛና ደራሲ አበራ ለማን የሕይወት ታሪክ የያዘው ይህ መጽሐፍ ዛሬ በብሔራዊ ቤተ መጻሕፍትና ቤተ መዛግብት የምረቃ መርሃ ግብሩ ይከናወናል፡፡ መጽሐፉ የደራሲውን የሕይወት ውጣ ውረድ፣ በኢትዮጵያ ሬዲዮና ፕሬስ መምሪያዎች የነበረውን ቆይታ እንዲሁም የሥነ-ጽሑፍ ጉዞውን በሰፊው ይዳስሳል።
በሌላ መረጃ “ABINA” የተሰኘ የአፋርኛ ሰዋሰው መጽሐፍ ለንባብ በቅቷል። የአፋርኛ ቋንቋ ሰዋሰው ክፍሎችን በተገቢው ሁኔታ እንዳካተተ የተነገረለት ይህ መጽሐፍ በአሊ አብዱልቃድር መዘጋጀቱ ተሰምቷል፡፡ አዘጋጁ ካሁን ቀደም የአፋርኛ ቋንቋ ድምጾችን፣ ምዕላዶችን እና የቋንቋን ጠባያት የሚተነትኑ መጽሐፍትን በማሳተም ለአንባብያን አድርሷል፡፡
መታሰቢያና የኪነ ጥበብ ውይይት
የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ የብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደ ሥላሴ ሥነ ጥበባት ማዕከል፣ የሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅንን 20ኛ ዓመት የዕረፍት መታሰቢያ ዝግጅት ዛሬ ያካሄዳል፡፡
በዝግጅቱ ላይ የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነብዩ ባዬ የሎሬት ጸጋዬ ቴአትሮች ላይ ዳሰሳ ያቀርባሉ፡፡ ወንድወሰን አዳነ (የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህርና ረዳት ፕሮፌሰር) ግጥሞቹን ይተነትናል፡፡ የሥነ ጽሑፍ ሐያሲው ቴዎድሮስ አጥላው በጸጋዬ ሕይወት ዙሪያ የተጻፈውን “ምጥቀት በቅኔ አክናፍ” የተሰኘው መጽሐፍ ላይ ዳሰሳ ያቀርባል ተብሏል፡፡
መርሃ ግብሩ የሚካሄደው የኢትዮጵያ ሳይንስ አካዳሚ ቅጥር ግቢ (ጳውሎስ ሆስፒታል አካባቢ) ንግድ ባንክ ጉለሌ ቅርንጫፍ አለፍ እንዳሉ ሲሆን ሰዓቱ 8፡00 ሰዓት ነው፡፡
የንባብና የሐሳብ ውይይት
በዛሬው ዕለት “ንባብ እና ዲጂታል ኤጅ” በሚል ሐሳብ ውይይት ይደረጋል። ውይይቱ የሚደረገው ዛሬ ከቀኑ 8፡00 ሰዓት ጀምሮ ሲሆን፤ የውይይት መነሻ ሐሳብ የሚያቀርበው ደራሲ ቡርሃን አዲስ (መሐመድ አሊ ቡርሃን) ነው፡፡ ውይይቱ የሚደረገው ደግሞ 4 ኪሎ ኢክላስ ሕንፃ ዋልያ መጻሕፍት አዳራሽ ነው፡፡
የሥዕል አውደ ርዕይ
7 ሰዓሊያን የተሳተፉበት “ዓድዋ” የተሰኘ የቡድን የሥዕል አውደ ርዕይ በእይታ ላይ ይገኛል፡፡ አውደ ርዕዩን ያዘጋጁት አኑማ ኃይሉ፣ የሱቃል ተስፋዬ፣ ዮርዳኖስ ውቤ፣ እዮብ እሸቱ፣ ሱራፌል ከተማ፣ ዮዲት ወልደማርያም እና ዘካሪያስ ከተማ ናቸው፡፡ ፈንድቃ የባህል ማዕከል እና ሀያት ረጀንሲ ሆቴል በመተባበር ያዘጋጁት ይህ መርሃ ግብር እስከ የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም በእይታ ላይ ይቆያል፡፡
የቡና ፌስቲቫል
በዛሬው የኢትዮጵያ የቡና ባህል ቀን ፌስቲቫል በዓድዋ ድል መታሰቢያ ሙዚየም ይካሄዳል፡፡ ኢትዮጵያ የቡና መገኛ ብቻ ሳትሆን፣ ለዓለም ልዩ የሆነ የቡና ሥነ-ሥርዓት ባህል ያበረከተች ሀገር ናት። ይህንን የቆየ ማኅበራዊ መስተጋብር ለማክበርና ይበልጥ ለማስተዋወቅ የተዘጋጀው ፌስቲቫል ዛሬ ለ2ኛ ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ዋና ዓላማውም ከመዝናናት ባለፈ የሀገራችንን የቡና ሥነ-ሥርዓት ባህል ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍ፣ ለዓለም ለማስተዋወቅና በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰስ ቅርስ ሆኖ እንዲመዘገብ ግፊት ለማድረግ እንደሆነ ተገልጿል፡፡
የቴአትር መርሃ ግብር
በመዲናችን አዲስ አበባ ቅዳሜ እና እሁድ የተለያዩ ቴአትሮች ይታያሉ። ቅዳሜ ከ11፡30 ሰዓት ጀምሮ “12ቱ እንግዶች” ቴአትር ይታያል፡፡ እሁድ በ7፡30 ሰዓት “ንጉሥ አርማህ” ቴአትር፣ እንዲሁም “እምዬ ብረቷ” የተሰኘው ቴአትር በ11፡30 ሰዓት ላይ ይታያሉ፡፡ በብሔራዊ ቴአትር በሌሎች ቀናት ደግሞ ሐሙስ 11፡30 ሰዓት “ሸምጋይ” እንዲሁም አርብ 11፡30 ሰዓት “ዴጊያ” ቴአትር ለእይታ ይበቃሉ፡፡
በጊዜው አማረ