የየካቲት ፈርጦች- የአድዋ ድል እና የጥቁሮች ታሪክ ወር

You are currently viewing የየካቲት ፈርጦች- የአድዋ ድል እና የጥቁሮች ታሪክ ወር

AMN – የካቲት 19/2018 ዓ.ም

የካቲት በኢትዮጵያ የታሪክ አቆጣጠር የድል ዋዜማና የድል ወር ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ ደግሞ በተለይ በሰሜን አሜሪካ የጥቁር ሕዝቦች የታሪክ ወር ተብሎ የሚከበርበት ልዩ ወቅት ነው። የካቲት ወር እና የአድዋ ድል ለጥቁር ሕዝብ ሥነ-ልቦናዊ ነፃነት ያላቸው ቁርኝት እጅግ ጥልቅ መሆኑ ይነገራል።

ይህ ወር እንዲከበር የታሪክ ምሁሩ ካርተር ጂ ዉድሰን ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል። መጀመሪያ እ.ኤ.አ በ1926 የጥቁሮች ታሪክ ሳምንት ተብሎ የተጀመረ ሲሆን፣ የካቲት ወር የተመረጠበት ክምንያትም ለጥቁሮች መብት የታገሉት የአብርሃም ሊንከን እና የፍሬድሪክ ዳግላስ ልደት በዚህ ወር ስለሚውል ነው።

በኋላም በ1976 ፕሬዝዳንት ጄራልድ ፎርድ ወሩን በይፋ የጥቁሮች ታሪክ ወር ብለው እንዳወጁት የታሪክ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡

የአድዋ ድል ጥቁር ሕዝቦች ነጭ ወራሪን ማሸነፍ እንደሚችሉ በተግባር ያሳዩበት የመጀመሪያው ታላቅ ድል ነው። ይህ ድል የአጋጣሚ ሳይሆን የተቀናጀ ወታደራዊ ስልት፣ የዲፕሎማሲ ጥበብ እና የአንድነት ውጤት ነው።

በዓለም ዙሪያ ለሚገኙ ጥቁር ሕዝቦችም እኛም ማሸነፍ እና ራሳችንን ማስተዳደር እንችላለን የሚል የተስፋ ብርሃን ሆኗቸዋል።

የአድዋ ድል ለፓን-አፍሪካኒዝም እንቅስቃሴ መወለድ ትልቁ መሠረት ነው። ብዙ የአፍሪካ አገራት የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ቀለማት ለባንዲራቸው መምረጣቸው የዚህ ትስስር ውጤት ነው።

በጥቁሮች ታሪክ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የሚለው ስም ለፖለቲካዊ ንቅናቄ ትልቅ ቦታ ያለው ሲሆን፣ በጭቆና ውስጥ የነበሩ ጥቁሮች አድዋንና ያልተገዛችውን ኢትዮጵያን እንደ መንፈሳዊ ጥንካሬ ይቆጥሩ ነበር።

የአድዋ ድል ለታዋቂ የጥቁር ሕዝብ መብት ተሟጋቾች ታላቅ ሥነ-ልቦናዊ መከታ ሆኖ አገልግሏል፡፡

ማርከስ ጋርቪ ኢትዮጵያን የአፍሪካዊያን ኩራት በማለት ኢትዮጵያ ሆይ ተነሺ በሚሉ መዝሙሮች የጥቁር ሕዝብን ሞራል ይገነባ ነበር።

ዶ/ር ማርቲን ሉተር ኪንግ ኢትዮጵያን እንደ የነፃነት ተስፋ ይመለከታት የነበረ ሲሆን፣ አድዋ ጥቁር ሕዝብ በታሪክ ውስጥ ባሪያ ብቻ ሆኖ እንዳልኖረ ማረጋገጫ እንደሆነውም ገልጿል።

የአድዋን ድል እንደ አንድነት ውጤት የሚመለከተው ማልኮም፣ ኢትዮጵያዊያን ያሸነፉት በዘር ሳይከፋፈሉ እንደ አንድ ጥቁር ሕዝብ ስለቆሙ ነው የሚለውን ትምህርት ያስተምር እንደነበር መረጃዎች ያመላክታሉ፡፡

የካቲት እና አድዋ ያላቸው የታሪክ አጋጣሚ ጥልቅ ነው። አድዋ ለጥቁሮች ታሪክ ወር ተጨባጭ የድል ማረጋገጫ ሲሆን፣ የጥቁሮች ታሪክ ወር ደግሞ ለአድዋ ድል ዓለም አቀፋዊ እውቅናን የሚሰጥ ክስተት ነው።

በአጠቃላይ አድዋ የአካል ነፃነትን ሲያበስር፣ የካቲት ደግሞ የአእምሮ ነፃነትን በማጠናከር ጥቁር ሕዝብ አንገቱን ቀና አድርጎ እንዲጓዝ የሚያደርግ የክብር ወር ነው።

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review