አድዋ የትውልድ ኩራትና የባንዳነት ሽንፈት የታየበት የታሪክ አውድ ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

You are currently viewing አድዋ የትውልድ ኩራትና የባንዳነት ሽንፈት የታየበት የታሪክ አውድ ነው- ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ

AMN- የካቲት 23/2018 ዓ.ም

130 ኛው የአድዋ ድል በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተከበረ ይገኛል።

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በበዓሉ ባደረጉት ንግግር የአድዋ ድል የትውልድ ኩራትና የባንዳነት ሽንፈት የታየበት የታሪክ አውድ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ኢትዮጵያ በታሪኳ የውጭ ወራሪዎችን ድል ያደረገችው በአንድነት በመቆሟ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ ዛሬም ያንን አንድነት በመድገም ሀገራዊ ሉዓላዊነትን ማስከበር እንደሚገባ ጥሪ አቅርበዋል።

የሃይማኖት አባቶችና ያልታጠቁ ዜጋዎች ሳይቀሩ ለሀገር ነፃነት የከፈሉት መስዋዕትነት ለዛሬው ትውልድ አርአያ መሆኑን ጠቅሰዋል።

በታሪክ ባንዳነት በማህበረሰቡ ዘንድ የሚወገዝ ተግባር እንደነበረ በማስታወስም፣ ዛሬም ለጠላት ተቀጥሮ ሀገርን ለማፍረስ የሚሰሩ ግለሰቦችን በንቃት መመከት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት በአድዋ አርበኞች መንፈስ በመመራት፣ የላኪና የተላላኪዎችን (ባንዳዎችን) ህልም እያመከነ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

ማንኛውም የመብት ጥያቄ ያለው ዜጋ ጥያቄውን ማቅረብ ያለበት የሀገርን ህልውና በማይጎዳ መልኩ መሆን እንዳለበትና ክፍተቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በመነጋገር መፍታትና ለጠላት ክፍተት አለመስጠት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።

ኢትዮጵያ ካለችበት ወቅታዊ ፈተና ለመውጣት የውስጥ እንክርዳዶችን በማጽዳትና እንደ አድዋ ዘመን በአንድነት በመቆም፣ ክብሯን ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባም አሳስበዋል።

የኢትዮጵያ የነጻነት ተምሳሌትና የጥቁር ህዝቦች ኩራት የሆነው የ130ኛው የአድዋ ድል በዓል፣ ከፍተኛ የመንግስት ሃላፊዎች፣የአፍሪካ ሀገራት የመከላከያ ሚኒስትሮችና ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በታላቅ ወታደራዊና ህዝባዊ ሥነ -ስርዓት በድምቀት እየተከበረ ይገኛል።

በታምራት ቢሻው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review