AMN – የካቲት 30/2018 ዓ.ም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት ቆይታ የከተማዋን የንግድ፣ የኢንዱስትሪና የቱሪዝም አቅም ለማሳደግ ታቅደው እየተከናወኑ ያሉ የልማት እንቅስቃሴዎችን ጎብኝተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በጉብኝታቸው ወቅት እንደተናገሩት ድሬዳዋ ከ400 በላይ ፋብሪካዎች የሚገኙባት የኢንዱስትሪ ከተማ መሆኗን ገልጸው፣ ነባር የኢንዱስትሪ ፓርኮችን ከነፃ ንግድ ቀጠና ጋር በማቀናጀት የገቢና ወጪ ንግድን ለማቀላጠፍ ሰፊ ሥራ እየተከናወነ እንደሚገኝ አስረድተዋል።
በተለይም በጨርቃጨርቅ፣ በኮንስትራክሽን ግብዓቶችና በኤሌክትሮኒክስ ዘርፎች የተጀመሩ ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ያመለከቱ ሲሆን፣ የነዳጅና የኮንስትራክሽን ቁሳቁስ መፈተሻ ጣቢያዎችን በማስፋፋት ለንግድ እንቅስቃሴው ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጠር ገልጸዋል።
የከተማዋን ተፈጥሯዊ አቀማመጥ አስመልክተው ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ በድሬዳዋ ዙሪያ የሚገኙ ተራራዎች ለከተማዋ ውበትና ለቱሪስት መስህብነት ያላቸው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ጠቁመዋል።
ሆኖም እነዚህ ተራራዎች የጥፋት ምንጭ እንዳይሆኑ አስፈላጊው ጥንቃቄ ሊደረግ ይገባል፤ በተራራማ ቦታዎች ላይ የእርከን ሥራዎችን ማከናወንና ዛፎችን መትከል የጎርፍ አደጋን ለመከላከል ወሳኝ መሆኑን አስገንዝበዋል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም ህገ ወጥ ግንባታዎችን በማስቀረት፣ በዲዛይንና በእውቀት ላይ የተመሠረተ የተቀናጀ የከተማ ግንባታ ለቀጣዩ ትውልድ ሊተላለፍ እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል።
በሌላ በኩል ታሪካዊው የድሬዳዋ ቤተ-መንግሥት እንደ “ገበታ ለሀገር” ፕሮጀክቶች ሁሉ በከፍተኛ ጥራት ታድሶ ለቱሪዝምና ለተለያዩ አገልግሎቶች ዝግጁ መደረጉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታውቀዋል።
ቤተ-መንግሥቱ ለግል ዘርፍ ተሰጥቶ ለሰርግ፣ ለስብሰባና ለተለያዩ ማኅበራዊ ዝግጅቶች አገልግሎት እንዲውል መደረጉን የገለጹ ሲሆን፣ ይህም ድሬዳዋን በክረምት ወቅት ከአዲስ አበባ ቅዝቃዜ ለሚሸሹ ጎብኚዎችና ለኮንፈረንስ ቱሪዝም ተመራጭ ያደርጋታል ብለዋል።
በመጨረሻም የከተማዋ አመራሮችና ነዋሪዎች ድሬዳዋን ለቱሪስትና ለኢንቨስትመንት ይበልጥ ምቹ የማድረግ ተግባራቸውን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ አቅርበዋል።
በበረከት ጌታቸው