AMN -መጋቢት 5/2018 ዓ.ም
ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለማንሳት ነገሮች እየተመቻቹለት የሚገኘው አርሰናል በ30ኛ ሳምንት መርሃግብሩ ኤቨርተንን ኤምሬትስ ላይ ይገጥማል።
አንድ ተጨማሪ ጨዋታ ቀድሞ ያከናወነው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ዛሬ ድል ከቀናው ተከታዩ ማንችስተር ሲቲ እስኪጫወት ልዩነቱን ወደ 10 ነጥብ ያሰፋል።
መድፈኞቹ ከኤቨርተን የሚገጥማቸው ፈተና ግን ቀላል አይሆንም።
የመርሲሳይዱ ክለብ በተለይ ባለፈው የውድድር ዓመት ሁለቱንም ጨዋታ አቻ በመለያየት የአርሰናል ዋንጫ የማንሳት ጉዞ ላይ መሰናክል ሆኖ ነበር።
ዘንድሮም በሂል ዲኪንሰን ስታዲየም ባደረጉት የመጀመሪያ ዙር ጨዋታ አርሰናል ተቸግሮ በቪክቶር ዮኬሬሽ የፍፁም ቅጣት ምት ግብ 1ለ0 ማሸነፉ ይታወሳል።
አርሰናል ፈተናው ከባድ ቢሆንም በየትኛውም መንገድ ሦስት ነጥቡን ለመውሰድ ይፋለማል ተብሎ ይጠበቃል።
ሁለቱ ቡድኖች በፕሪምየር ሊጉ 67 ጊዜ ተገናኝተው አርሰናል 39 ጨዋታዎችን አሸንፏል። ኤቨርተን ማሸነፍ የቻለው 12 ጨዋታዎችን ነው።
በዛሬው ጨዋታ በአርሰናል በኩል ማርቲን ኦዴጋርድ እና ሊአንድሮ ትሮሳርድ መሳተፋቸው አልተረጋገጠም።

በሌላ ጨዋታ ማንችስተር ሲቲ ዋንጫ የማሸነፍ ተስፋውን ለማለምለም ወደ ለንደን በማቅናት ዌስትሃም ዩናይትድን ይገጥማል።
በሳምንቱ አጋማሽ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ በሪያል ማድሪድ 3ለ0 የተሸነፈው ሲቲ ዌስትሃም ላይ ያለው የበላይነት ከፍ ያለ ነው።
ሲቲ ከዌስትሃም ዩናይትድ ጋር ያደረጋቸውን ሰባት የመጨረሻ የፕሪሚየር ሊግ ጨዋታዎች በሙሉ አሸንፏል።
የፔፕ ጋርዲዮላው ቡድን ከዋንጫ ፉክክሩ ላለመራቅ ምሽት 5 ሰዓት የሚጀምረውንም ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅበታል።
ለፔፕ ጋርዲዮላ ትልቁ መሰናክል ግን የዌስትሃሙ አሰልጣኝ ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ ናቸው። ፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ በሊግ ጨዋታ አራት ጊዜ ጋርዲዮላን አሸንፈዋል።
ስፔናዊ አሰልጣኝ በሊግ ጨዋታዎች በየርገን ክሎፕ አምስት ጊዜ የተረታበት ከፍተኛ ሽንፈቱ ነው። ከዚህ በመቀጠል ነው ኑኖ ስፕሪቶ ሳንቶ የሚመጡት።
ዎልቭስን ፣ ቶተንሃም እና ኖቲንግሃምን እየመሩ የፔፕን ቡድን ያሸነፉት ኑኖ ይህን ታሪካቸውን በዌስትሃም መድገም ይፈልጋሉ።
ሌላኛው ተጠባቂ ጨዋታ ቼልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ኒውካስትል ዩናይትድን ምሽት 2:30 የሚያስተናግድበት ነው።
በርንሌይ ከ ቦርንማውዝ እንዲሁም ሰንደርላንድ ከ ብራይተን በተመሳሳይ ምሸት 12 ሰዓት ላይ ይጀምራሉ።
በሸዋንግዛው ግርማ