AMN – መጋቢት 7/2018 ዓ.ም
በሀገራችን ለዘመናት የቆዩና ለግጭት መንስኤ የሆኑ ቅራኔዎችን በዘላቂነት ለመፍታት ታላቅ ተስፋ የተጣለበት ሀገራዊ ምክክር፣ በፖለቲካ መሪዎች፣ በመንግስት እና በማህበረሰብ ተወካዮች መካከል የሚደረግ ወሳኝ የዲሞክራሲ ሂደት መሆኑ ይታወቃል።
ይህ ሂደት በተለይም ስር የሰደዱ አለመግባባቶችን በጠረጴዛ ዙሪያ በንግግር ለመፍታት አበክሮ የሚሰራ ቢሆንም፣ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ በፈቃደኝነት ወይስ በግዴታ ሊሆን ይገባል የሚለው ነጥብ የሂደቱን መብትና ኃላፊነት ለመረዳት ወሳኝ ነው።
ምክክር በተፈጥሮው ሰብዓዊነትን በማስቀደም እና መተማመንን መሰረት በማድረግ የሌላውን ችግር ለመረዳት ቅን ልብን የሚሻ ተግባር በመሆኑ፣ በግዴታ የሚካሄድ ምክክር የሚፈለገውን ፍሬ እንደማያፍራ ይታመናል።
ሂደቱ እንደሌሎች አስተዳደራዊ ተግባራት በተጻፉ ህጋዊ ማዕቀፎች ብቻ ከመመራት ይልቅ፣ በሰው ልጆች እኩልነት በማመን ማንኛውም ዜጋ በግልም ሆነ በቡድን ለሀገሩ ሊያበረክት የሚችለውን አስተዋጽኦ አጉልቶ ለማሳየት ይሰራል::
ይህም ተሳትፎው ከህግ አስገዳጅነት ይልቅ በባለድርሻ አካላት ፍላጎት ላይ እንዲመሰረት ያደርገዋል።
የሌሎች ሀገራት ተሞክሮዎች እንደሚያሳዩት፣ የምክክር ሂደቶች የታለመለትን ግብ እንዳይመቱ ከሚያደርጉ ተጠቃሽ ምክንያቶች መካከል አንዱ የባለድርሻ አካላት ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆንና ለሂደቱ ምቹ መደላድል አለመፈጠሩ ነው።
ምንም እንኳን በምክክር ሂደት ላይ መሳተፍ በህግ የተጣለ ግዴታ ባይሆንም፣ ከሂደቱ መታቀብ ግን የከፋ መዘዝ እና የታሪክ ተጠያቂነትን ይዞ ሊመጣ እንደሚችል መገንዘብ አስፈላጊ ነው።
በርካታ ባለድርሻ አካላት ከምክክር መድረኮች ራሳቸውን ሲያገሉ መፍትሄ ያልተገኘላቸው አለመግባባቶች ተባብሰው ለሰው ህይወት መጥፋትና ለሀገር ቀውስ ምክንያት ሲሆኑ ይስተዋላል።
ሀገራዊ ምክክር ሌሎች ተቋማት ሊያስተናግዷቸው የማይችሏቸውን ውስብስብ ጉዳዮች ለማስተናገድ የሚያስችል ብቸኛ የዲሞክራሲ አጋጣሚ ተደርጎ ይወሰዳል።
ይህ ሂደት ለአለመግባባት መንስኤ በሆኑ ጉዳዮች ላይ በባለድርሻ አካላት መካከል ግልጽ ውይይት እንዲደረግ መንገድ ከመጥረጉም በላይ፣ ከፍተኛ ወጪ ከሚጠይቁና አውዳሚ ከሆኑ ጦርነቶች ይልቅ በአጭር ጊዜና በትንሽ ወጪ የመግባባት ድልድይ ይገነባል።
በተጨማሪም ባለድርሻ አካላት ባልተግባቡባቸው ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በመደማመጥ እርስ በእርስ መተማመንን እንዲያጎለብቱ በማድረግ፣ ለዘመናት ለቆዩ መሰረታዊ ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ የሚሆኑ ሀሳቦች እንዲመነጩ ምቹ መደላድል ይፈጥራል።
በመሆኑም ባለድርሻ አካላት በሂደቱ ንቁ ተሳትፎ ማድረግ ዛሬ ላለው ቀውስ መፍትሄ ከመፈለግ ባለፈ፣ ነገ ለሚገነባው የሰላም ጎዳና ጉልህ ድርሻ እንደሚኖረው የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ለአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ የላከው መረጃ ያመላክታል።