AMN መጋቢት 9/2018 ዓ.ም
የሃይማኖት አባቶች እና ምዕመናን ለቤተ ክርስቲያንም ሆነ ለሃገር የማይጠቅሙ ግጭት ፈጣሪ እሳቤዎችን እና ድርጊቶችን በመከላከልና ተጠያቂነትን በማስፈን ሃይማኖታዊ አንድነታቸዉን ሊያጠናክሩ እንደሚገባ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር “የሃይማኖት ተቋማት በመደመር መንግስት እይታ” በሚል መሪ ሀሳብ ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን የእምነት አባቶች ጋር ዉይይት አካሄዷል፡፡
የሃይማኖት አባቶቹን ያወያዩት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከሰላም እና የህግ የበላይነትን ከማረጋገጥ ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ምላሽ እና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
የሃይማኖት ተቋማትም ሆኑ የሃይማኖት አባቶች ለሃገራዊ ሰላምና ልማት መረጋገጥ ትልቅ ድርሻ እና ሃላፊነት እንዳለባቸዉ ያነሱት ከንቲባ አዳነች አቤቤ ቤተ እምነቶች ሰላምን ሊሰብኩ እና የሰላም አምባሳደር ሊሆኑ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች የተከሰቱ የጸጥታ ችግሮችና ግጭቶች እንዲቆሙ ከመጠየቅና ከማዉገዝ ባለፈም የሃይማኖቶች አባቶች እና ምዕመናን ግጭትን በእሳቤም ሆነ በተግባር ከመደገፍ እንዲቆጠቡ ማስተማር ይገባል ነዉ ያሉት፡፡
ግጭት ሲፈጠር ተከታትሎ በማዉገዝ ብቻ ዘላቂ ሰላምን ማረጋገጥ ስለማይቻል የሃይማኖት አባቶች የግጭት መንስኤዎችን ከስር መሰረታቸዉ ለማድረቅ ከመንግስት ጋር በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ግጭት ፈጣሪዎቹ ጥቂት ቢሆኑም የሚገኙት ግን በብዙሃኑ መካከል ነዉ፡፡
መንግስት ግጭቶች በተከሰቱባቸዉ አካባቢዎች ህግ የማስከበር ስራ እየሰራ ነዉ ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የተጀመረዉ ህግ የማስከበር ስራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡
የሃይማኖት ተቋማት ግጭት እንዲወገድ ከማስተማር ጀምሮ፤ ትዉልዱን በመልካም ስነ ምግባር ማነጽና ግጭት ፈጣሪዎችን መታገል እንደሚጠበቅባቸዉም ጨምረዉ ገልጸዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቤተክርስቲያን ዉስጥ ከሚታዩ ክፍተቶች ጋር ተያይዞ ለተነሱ ጥያቄዎች በሰጡት ምላሽ በተቋም ዉስጥ የሚፈጠሩ ችግሮችን ዉስጣዊ አንድነትን በጠበቀ እና በሰለጠነ መንገድ ተነጋግሮ መፍታት ይገባል ብለዋል፡፡

መንግስት በቤተክርስቲያን የዉስጥ አሰራር ጣልቃ አይገባም፤ በጣልቃ ገብነት የሚፈታ ችግር የለም፤ የመንግስት ፍላጎት የሃይማኖት ተቋማት ዉስጣዊ አንድነት እንዲከበር ብቻ ነዉ ብለዋል ከንቲባ አዳነች አቤቤ፡፡
ለሃይማኖት ተቋምና ለሃገር የማጠቅሙ ችግሮች ካሉ ተነጋግሮ መፍታት ይገባል ያሉት ከንቲባ አዳነች አቤቤ የቤተ ክርስቲያኗ ህግና ስርአት ማክበር እና ዉስጣዊ ተጠያቂነትን ማስፈን እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
በሃይማኖት ሽፋን የሚደረጉ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችና ስርዓት አልበኝነትን ጨምሮ ሃገርንና ወገንን የሚጎዱ አግባብነት የሌላቸዉ ድርጊቶች ካሉ ግን መንግስት የህግ የበላይነትን ለማስከበር ይገደዳል፡፡
በወንድማገኝ አሰፋ