AMN- መጋቢት 12/2018 ዓ.ም
በነዳጅ አቅርቦት ዙሪያ በሚፈጸሙ ወንጀሎች ላይ የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ መቀጠሉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ።
በነዳጅ ስርጭትና ግብይት ሂደት ላይ የሚታዩ ሕገ-ወጥ ተግባራትን ለመቆጣጠር በስድስት ክልሎችና በሁለት የከተማ አስተዳደሮች የተጀመረው የተቀናጀ ዘመቻ መጠነ ሰፊ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑን ሚኒስትሩ ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ባለፉት ቀናት በተደረገው ከፍተኛ ክትትልና ቁጥጥርም የተለያዩ እርምጃዎች መወሰዳቸውን ሚኒስቴሩ ገልጿል።
በዚህ መሰረትም በሕገ-ወጥ መልኩ ሲዘዋወር የነበረ 250 ሺህ 221 ሊትር ቤንዚን እና 198 ሺህ 432 ሊትር ናፍጣ ተይዞ መወረሱን ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ከተወረሰው ነዳጅ መካከል በሽያጭ ለጥቅም እንዲውል ከተደረገው ውስጥ ከ48 ሚሊዮን 663 ሺህ ብር በላይ ለመንግሥት ገቢ መሆኑን ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን በአሻጥሩ ተሳትፈው የተገኙ 613 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስረድተዋል።
ከተያዙት ግለሰቦች መካከል የንግድ ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ የቡድን መሪዎች፣ የሬጉላቶሪ ባለሙያዎች፣ የነዳጅ ማደያ ባለቤቶችና ሠራተኞች እንዲሁም በየደረጃው የሚገኙ የጸጥታ አካላት እንደሚገኙበት ጠቁመዋል።
እርምጃው በታችኛው መዋቅር ላይ ብቻ ሳይሆን በውሳኔ ሰጪዎች ላይም ያነጣጠረ መሆኑን ገልጸው ይህ የተቀናጀ የቁጥጥር ሥራ በዘርፉ የሚታየውን አሻጥር በመቅረፍ ፍትሃዊ የነዳጅ ስርጭት እንዲኖር ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።
ያለውን ዓለም አቀፋዊ የነዳጅ ገበያ ተጨባጭ ሁኔታ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ነዳጅ አከፋፋዮችና ህብረተሰቡ ነዳጅን በቁጠባና በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት እንዲጠቀሙም ሚኒስትሩ ጥሪያ ማስተላለፋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።