“ድህነት ዕጣ ፈንታ አይደለም በአስተሳሰብ ለውጥ ማሸነፍ ይቻላል”

You are currently viewing “ድህነት ዕጣ ፈንታ አይደለም በአስተሳሰብ ለውጥ ማሸነፍ ይቻላል”

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በምግብ ዋስትና እና በብቃት የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ፕሮግራም ሲሳተፉ የነበሩ 15 ሺህ 492 ተጠቃሚዎችን ከተረጂነት ወደ ምርታማነት አሸጋገረ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን ማቲዎስ በመርሀ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት ድህነት ዕጣ ፈንታ አለመሆኑንና በአስተሳሰብ ለውጥ ማሸነፍ እንደሚቻል የግንዛቤና የመግባባት ሥራ በመሥራቱ ተጠቃሚዎች ለለውጥ ዝግጁ እንዲሆኑ ማድረግ ተችሏል ብለዋል።

አያይዘውም ድጋፉ በትክክል የሚገባቸውን የኅብረተሰብ ክፍሎች የመለየትና የማጥራት ሥራ በከፍተኛ ጥንቃቄ መከናወኑንና ይህም የመንግሥትና የለጋሾች ሀብት ለታለመለት ዓላማ ብቻ እንዲውል ማስቻሉን ገልጸዋል።

ተጠቃሚዎች ወደ ሥራ ከመሰማራታቸው በፊት አስፈላጊው የስነ-ልቦና የሕይወት ክህሎትና የንግድ ሥራ ሥልጠና እንዲያገኙ ተደርጓል ። ለዚህም እንደ መነሻ የሚሆን የገቢ ማስገኛ ሥራ ማስጀመሪያ ድጋፍ የተመቻቸላቸው ሲሆን ይህም ዜጎች በገበያው ውስጥ በራስ መተማመን እንዲንቀሳቀሱ አቅም ሆኗቸዋል።

በተጨማሪም ተጠቃሚዎች የሥራ ዕድል እንዲያገኙ ከመንግሥታዊ ተቋማት ባሻገር ከመንግሥታዊ ካልሆኑ ድርጅቶችና ከግል ዘርፉ ጋር የማቀናጀት ሥራ ተሠርቷል ።ይህም ተጠቃሚዎች ሰፊ የገበያ ትስስርና የቴክኒክ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ ሽግግሩን ይበልጥ አፋጥኖታል ።

የሴፍቲኔት ተጠቃሚዎች የሽግግር ሂደት በተመለከተ ለሦስት ዓመታት እንዲሁም የወጣቶች የሥራ ላይ ልምምድ ተሳታፊዎች ለዘጠኝ ወራት በቆይታቸው ያገኙትን ዕውቀትና የቆጠቡትን ካፒታል ይዘው ወደ ራሳቸው ቋሚ ሥራ መሸጋገራቸውን አረጋግጠዋል ።

በቀጣይም ቢሮው የሥራ ቦታዎችን በማመቻቸት፣ የብድር አገልግሎትን በማቀራረብና የቴክኒክ ድጋፍ በመስጠት ከተመራቂዎቹ ጎን መቆሙን እንደሚቀጥል ቃል ገብተዋል ።

ዘገባው የአዲስ አበባ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ነው ።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review