ለ47 የፖለቲካ ፓርቲዎች በ50 የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ተመደበላቸው

You are currently viewing ለ47 የፖለቲካ ፓርቲዎች በ50 የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ተመደበላቸው

AMN- መጋቢት 19 /2018 ዓ.ም

47 የፖለቲካ ፓርቲዎች በ50 የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ነፃ የአየር ሰዓትና የጋዜጣ አምድ ተመድቦላቸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እና የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል እጩዎች ነጻ የአየር ሰዓት ድልድል አድርገዋል።

ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በሚካሄደው ጠቅላላ ምርጫ የሚፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የግል ዕጩዎች ለምረጡኝ ቅስቀሳ የሚውል ነጻ አየር ሰዓት ድልድል የእጣ አወጣጥ ስነ ስርአትም እየተካሄደ ነው።

የነጻ የአየር ሰዓት ድልድሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አማራጭ ሃሳባቸውን በነፃነት ለህዝብ የሚያስተዋውቁበት መድረክ መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላትወርቅ ኃይሉ በእጣ ማውጣት ስነ ስርአቱ ላይ ተናግረዋል።

መራጩ ህዝብም በመረጃ ላይ የተመሰረተ ውሳኔ ይወስን ዘንድ ነጻ የአየር ሰዓቱ ከፍ ያለ ጠቀሜታ እንዳለውም ሰብሳቢዋ አብራርተዋል።

50 የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት ለተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ለግል እጩዎች ነፃ የአየር ሰአትና አምድ መመደባቸውን ያስታወቁት ደግሞ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሃይማኖት ዘለቀ ናቸው።

በቴሌቪዥን 513 ሰዓታት፣ በራዲዮ 782 ነጥብ 5 ሰዓታት እንዲሁም በጋዜጣ 576 አምዶች ለፖለቲካ ፓርቲዎችና ለግል እጩዎች መደልደሉ ተገልጿል።

24 ራዲዮ ጣቢያዎች፣ 20 የቴሌቪዥን ተቋማትና እና 6 ጋዜጦች የፖለቲካ ፓርቲዎችን ፖሊሲ በነፃ እንዲያስተናግዱ ተመድበዋል።

የነጻ የአየር ሰዓቱ ከመጋቢት 23 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እስከ ግንቦት 19 ቀን 2018 ዓ.ም የሚቆይ ሲሆን ቅዳሜ እና አሁድን ጨምሮ በበዓል ቀናት ነጻ የአየር ሰአቱን መጠቀም እንደማይቻል ተገልጿል።

በካሳሁን አንዱዓለም

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review