AMN ሐምሌ 24/2018

የሀገራዊ ምክክሩ አካል የሆነው የ500 ዋና ጉባኤ የፊታችን ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጀመር የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ ፣ የኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙሃን መግለጫ ሰጥተዋል።
ተመካካሪዎች በተለያዩ ቡድኖች ተከፋፍለው በስምንቱ አጀንዳዎች ላይ እየመከሩ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በአሁኑ ሰዓት የ250 ቡድኖች ውይይት እየተካሄደ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤የተወያዩባቸውን አጀንዳዎች ለ500 ጉባኤ እንደሚያቀርቡ አመልክተዋል።
የ250 ቡድኖች በቀጣይ ቀናት ሀሳቦችን በማብላላት ለ500 ጉባኤው የሚቀርቡ አጀንዳዎችን እንደሚያቀርቡም ተናግረዋል።
የ500ው ትልቁ ጉባኤ ሰኞ ሐምሌ 27 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚጀመርም ነው ዋና ኮሚሽነሩ የጠቆሙት።
የ500 ስብሰባው ይበልጥ የሀሳብ መቀራረብና መግባባትን ይፈጥራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ነው የገለጹት።
ዛሬ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው የውሳኔ አሰጣጥ ሂደት ላይ እገዛ የሚያደርጉ የክልል (ከተማ መስተዳደር) እና የፌዴራል ተወካዮች ምርጫ መደረጉን ጠቁመዋል።
በዚህም ተመካካሪዎቹ 330 የሚሆኑ ተወካዮችን መምረጣቸውን ነው ያነሱት።
ተመካካሪዎቹ የተለያዩ ሀሳቦችን ይዘው ቢመጡም ኢትዮጵያን ባስቀደመ ሁኔታ በሃላፊነት ስሜት በቁርጠኝነት እየተወያዩ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
አጠቃላይ ሂደቱ ተስፋ ሰጪ መሆኑንና አለመግባባቶችን በንግግር ለመፍታት ያለው ፍላጎት የሚበረታታ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ዋና ኮሚሽነሩ ህብረተሰቡ በማህበራዊ ሚዲያ ከሚተላለፉ ሀሰተኛ መልዕክቶች በመቆጠብ ኮሚሽኑ የሚያወጣቸውን ትክክለኛ መረጃ ብቻ እንዲከታተልም ጥሪ አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ከሐምሌ 8 ቀን 2018 ዓ.ም አንስቶ እየተካሄደ ይገኛል።