ከግብጾች ጋር ለዘመናት የተፋለሙት የላብ፣ የደም እና የውሃ ጠብታዎች

AMN – ሐምሌ 24/2018 ዓ.ም

ግብጾች ለረጅም ዘመናት የተጋጩትና የተፋለሙት ከኢትዮጵያውያን ጋር ብቻ አይደለም፤ ከተፈጥሮም ከፈጣሪም ጋር ተጋጭተዋል፡፡

ኢትዮጵያ ተፈጥሮ በቸረቻት ውሃ ለምን ትጠቀማለች? ለምን ትለማለች? ለምንስ ታድጋለች?

ግብጽ አባይን እንደ ብሔራዊ ደህንነት እና የህልውና ጉዳይ የምትቆጥረው ሲሆን፤ በውሃው ላይ ታሪካዊ መብት አለኝ የሚል የተሳሳተ አቋም በመያዝ ለዘመናት ኖራለች፡፡

ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዳትጠቀም የተለያዩ ጫናዎችን ከማሳረፍ አልፋ የህዝቧን የኃይልና የልማት ፍላጎት እንዳታሟላ በአለም አደባባይ ፊት ለአመታት ተፋልማለች፡፡

በአባይ ወንዝ ላይ ያላትን ፍጹም የሞግዚትነትና የባቤትነት ይገባኛል ጥያቄ ለማስከበርም የቅኝ ግዛት ስምምነቶችን በማስረጃነት ይዛ በአለም አደባባይ ፊት ኢትዮጵያን በተደጋጋሚ ከሳለች፡፡

ኢትዮጵያ ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መገንባት ስትጀምር፣ ፕሮጀክቱ እንዳይሳካ የተለያዩ ጫናዎችን ስታደርግ ቆይታለች፡፡

የዓለም ባንክ እና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤትን ጨምሮ የተለያዩ አለም አቀፍ ተቋማትን ደጅ በመጥናት ኢትዮጵያ በአባይ ላይ የምታደርገው የልማት ስራ ህገ-ወጥ እና የቀጠናውን ሰላም አደጋ ላይ የሚጥል ነው በማለት ከፍተኛ የዲፕሎማሲ ጫናዎችን ስትፈጥር ኖራለች፡፡

ግድቡ በታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ላይ ከፍተኛ የውሃ እጥረት ያስከትላል የሚል ያልተረጋገጠ የፈጠራ ስጋትን በማንሳት እንዲሁም ኢትዮጵያ የዓለም አቀፍ ህግ ጥሳለች የሚል ሃሰተኛ ክስ በመመስረት በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን፣ በተቀጠሪና ተከፋይ አክቲቪስቶች የኢትዮጵያን ስም ስታጠለሽ ኖራለች፡፡

የግብጾች ብሔራዊ ጥቅም የሚረጋገጠው ኢትዮጵያን በማዳከም፣ በማፈራረስና በማጥፋት የሚል ነዉ ሃሰተኛና አደገኛ ትርክት ለገዛ ዜጎቻቸው በማስተማርና በመንገር በኢትዮጵያና በእትዮጵያውያን ላይ የተለያዩ ደባዎችን ለአመታት ፈጽመዋል፡፡

ኢትዮጵያ በበኩሏ ፍትሃዊ እና ምክንያታዊ የውሃ አጠቃቀም መርህን በመከተል፣ ተፈጥሮ በቸረቻት እና ከገዛ መሬቷ በሚመነጭ ውሃ ዜጎቿን ከድህነት ለማውጣት እንደምትሻ የተለያዩ ዲፕሎማሲያዊ ስራዎችን ስታከናውን ኖራለች፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሃይል ከማመንጫ ውጪ የውሃ ፍሰትን እንደማያስተጓጉል፣ ይልቁንም ለሱዳን እና ለግብጽ የጎርፍ አደጋን በመከላከል ለሀገራቱ ትልቅ ውለታ እንደሚሆን በተደጋጋሚ መክራለች፡፡

ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ሀብቷ እንዳትጠቀም፣ እንዳትለማ እና ዘላቂ ሰላም እንዳታገኝ ግብጽ ለረጅም ዘመናት ብታሴርም ኢትዮጵያውያን ግን የላብ፣ የደም እና የውሃ ጠብታ በመክፈል ጉባ ላይ ዘመን የማይሽረውን የአድዋን ታሪክ ዳግም ተጋርተዋል፡፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በመገደቡ ምክንያት ግብጾች ለዘመናት ሲተርቱ እንደኖሩት በሱዳን፣ በግብጽ እና በታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት ላይ የደረሰ አንዳችም የውሃ ዕጥረት የለም፤ ይልቁንም ግድቡ ኢትዮጵያን ጨምሮ ለቀጣናው ሀገራት ትልቅ የብርሃን ምንጭ ሆኗል፡፡

በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ጭምር ጣልቃ በመግባት እና ፀረ-ሰላም ሃይሎችን በማደራጀት፣ በማስታጠቅና በርካታ ሚሊዮን ዶላሮችን በመመደብ ኢትዮጵያውያንን በብሄርና በሃይማኖት አጀንዳዎች እርስ በርስ እንዲጋጩ ለአመታት ስታሴር የኖረችዉ ግብጽ፤ ዛሬም ህገወጡን የህወሃት ቡድንን ጨምሮ ሻዕቢያና ሌሎች የጸረ ሰላም ሃይሎችን በማደራጀትና በማስተባበር በቀጣናዉ ሌላ ግጭትና ጦርነት ለመፍጠር ማቀዷን የፖለቲካ ተንታኞች በመናገር ላይ ይገኛሉ፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review