AMN – መጋቢት 21/2018 ዓ.ም
ወደ ሀገር ውስጥ እየገቡ ያሉ አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሞዴሎች የኢትዮጵያን የአረንጓዴ ጉዞ ሽግግር በማፋጠን ረገድ ከፍተኛ ሚና እንደሚጫወቱ ዥንዋ ዘግቧል።
በቻይናው ጓንግዙ አውቶሞቢል ግሩፕ የተመረቱትን እነዚህን አዳዲስ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ሞዴሎች ለገበያ ለማቅረብ ደንበኞችን የማስተዋወቅ መርሃ ግብር ሰሞኑን በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስትር ዓለሙ ስሜ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ መንግስት የትራንስፖርት ዘርፉን ወደ አረንጓዴ ጉዞ ለማሸጋገር እና ወደ አየር የሚለቀቀውን መርዛማ የካርቦን ልቀት ለመቀነስ ወሳኝና ተግባራዊ እርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም ይህም በኢኮኖሚ ረገድ ተቋቋሚ የሆነና ለአካባቢ ጥበቃ የበኩሉን አስተዋጽኦ የሚያበረክት የትራንስፖርት ሥርዓት ለመገንባት የተወሰደ እርምጃ መሆኑን ገልጸዋል።

ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ የአፍሪካ የመኪና ማምረቻ ማዕከል ለመሆን እየሰራች መሆኑን ጠቅሰው፤ ያላትን የኃይል ሀብት፣ የወጣቱን የሰው ኃይል እና የሰለጠነ ጉልበት በመጠቀም የአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ስትራቴጂን ለማሳካት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
ይህም የኢትዮጵያ መንግስት የሀገሪቱን የአረንጓዴ ጉዞ ለማሳካት ያለውን ከፍተኛ ቁርጠኝነት የሚያሳይ ሲሆን፤ የአካባቢ ብክለትን የሚቀንሱና ለአጠቃቀም ምቹ የሆኑ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በማስገባት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የዥንዋ ዘገባ አክሎም፤ የኢትዮጵያ መንግስት ካለፉት ጥቂት ዓመታት ወዲህ ከፍተኛ የኢንዱስትሪ መስፋፋትን እያስመዘገበ ከመሆኑ ባለፈ መሰረተ ልማቶችን በማስፋፋትና የውጭ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የትራንስፖርት ሽግግርንና አነስተኛ የካርቦን ልቀት ያለውን ኢኮኖሚ ለመገንባት እንዲሁም ለአዳዲስ የኃይል ተሽከርካሪዎች ኢንዱስትሪ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር ረገድ አስደናቂ ስራዎችን እየሰራ እንደሚገኝ አስታውሷል።
በመልካሙ አበበ