በጊዜው አማረ
አዲስ አበባ ስሟን መመጠን ከጀመረችባቸው ጥቂት ዓመታት ወዲህ፣ ከተማዋን የሚያውቃት ሰው እንኳን ሊያስታውሳት እስከሚቸገር ድረስ በከፍተኛ ፍጥነት እየተለወጠች ትገኛለች። “አሮጌውን በማፍረስ አዲሱን መተካት” ብቻ ሳይሆን፣ ነባሩን ማንነት ከዘመናዊነት ጋር የማጣመር ጥበብ የታየበት ይህ የለውጥ ጉዞ፣ መዲናዋን በአፍሪካ መድረክ ያላትን ተሰሚነት በውበቷም እንዲደገፍ እያደረገው ነው። ይህ ለውጥ ከተማዋን ለነዋሪዎቿና ለጎብኚዎች ምቹ የሆነች የመኖሪያና የሽርሽር እንድትሆን አድርጓታል።
የከተማዋ አዲስ ገጽታ በተለይ በኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች አማካኝነት የተገለጠ ሲሆን፣ ሰፋፊ፣ ለእግረኛ እና ተሽከርካሪ ምቹ የሆኑ መንገዶች የአዲስ አበባን የከተማ ልማት ደረጃ ከፍ አድርገውታል። እነዚህ በዘመናዊ መብራቶችና በአረንጓዴ ተክሎች መታጀባቸው፣ ከተማዋ በቀንም ሆነ በሌሊት እኩል ውበት እንዲኖራት አስችሏታል። ይህ የመሰረተ ልማት ግንባታ የከተማዋን የትራፊክ ፍሰት ከማሳለጡ ባለፈ፣ ነዋሪው በነፃነት ወጥቶ እንዲንሸራሸርና በከተማው እንዲኮራ የሚያደርግ ሥነ-ልቦናዊ ለውጥ አምጥቷል ማለት ይቻላል።
ባለፉት ጥቂት ዓመታት የተገነቡት ግዙፍ የመዝናኛ ፓርኮች አዲስ አበባን ውብ ከማድረግ ባለፈ፣ ከተማዋን “የአረንጓዴነት” ተምሳሌት አድርገዋታል። በፋውንቴን ከታጀቡ የመዝናኛ ፓርኮች በተጨማሪ እንደ አንድነትና እንጦጦ ፓርኮች እንዲሁም ወዳጅነት አደባባይ ያሉ ስፍራዎች ተፈጥሮን ከታሪክና ከዘመናዊ ጥበብ ጋር አጣምረው የያዙ በመሆናቸው፣ ለመዲናዋ ነዋሪዎችና እንግዶች ዋነኛ የመዝናኛ አማራጭ ሆነዋል። እነዚህ ስፍራዎች ነዋሪዎች ጊዜ የሚያሳልፉባቸው፣ ወጣቶች የሚዝናኑባቸውና የውጭ ሀገር ዜጎች የኢትዮጵያን እንግዳ ተቀባይነትና ውበት የሚመሰክሩባቸው የቱሪዝም ማዕከላት ሆነው እያገለገሉ ይገኛሉ።
ይህ አስደናቂ ለውጥና ውበት በርካታ ታዋቂ የፖለቲካ መሪዎችን፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎችንና ዲፕሎማቶችን ቀልብ እየሳበ ይገኛል። አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ትልልቅ አህጉርና ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በብቃት የምታስተናግድ ብቻ ሳትሆን፣ መሪዎች በትርፍ ጊዜያቸው በፓርኮቿ ተዝናንተውና በውብ ጎዳናዎቿ በእግር ተጉዘው ስለለውጧ የሚመሰክሩላት ከተማ ሆናለች። ይህ ደግሞ የከተማዋን ዲፕሎማሲያዊ ተሰሚነትና የቱሪስት ፍሰት በከፍተኛ ደረጃ እንዲጨምር አድርጎታል።
ባለፉት ዓመታት በመዲናዋ የታየው ውበትና ጽዳት የዓለም አቀፍ ዝነኞችን ትኩረት የሳበ ሆኗል። ዓለም አቀፍ የጥበብ ሰዎች የከተማዋን አዲስ ገጽታ እንደ ስራዎቻቸው መነሳሻ እየተጠቀሙበት ይገኛሉ። በዘመናዊ የግድግዳ ስዕሎች (Murals) ያጌጡ ጎዳናዎች፣ የጥበብ ጋለሪዎችና ለኪነ-ጥበብ ስራዎች ምቹ የሆኑ ክፍት ቦታዎች መበራከታቸው፣ አርቲስቶችና የፈጠራ ባለሙያዎች ወደ መዲናዋ እንዲጎርፉ አድርጓል። አዲስ አበባ ዛሬ ላይ ለፊልም ቀረጻ፣ ለሙዚቃ ቪዲዮዎችና ለፎቶ ግራፍ ጥበብ ተመራጭ መዳረሻ ሆናለች፤ ይህም ከተማዋን የታሪካዊና ዘመናዊ ጥበብ መገናኛ አድርጓታል።
የከተማዋ ልማትና ለውጥ ለውበቷና ለመዝናኛ ተመራጭነቷ ትልቅ ድርሻ አበርክቷል። ቀደም ሲል የቆሻሻ መጣያና የመጥፎ ሽታ ምንጭ የነበሩ የወንዝ ዳርቻዎች ዛሬ ወደ ውብ የልማት ኮሪደሮችና የመዝናኛ ስፍራዎች መቀየራቸው፣ የአዲስ አበባን የጽዳት ደረጃ ወደ አዲስ ከፍታ አሳድጎታል።
ከ15 ዓመታት በላይ በአስጎብኝነት እየሰሩ የሚገኙት ወይዘሮ ሶስና ሙሉጌታ ቀደም ሲል ወደ አዲስ አበባ ለስብሰባና ለተለያዩ ጉዳዮች የሚመጡ እንግዶች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙ መጠየቅ አዳጋች፣ ጎብኝዎችም በከተማዋ እንደ ልብ የሚዝናኑባቸውና ጊዜ የሚያሳልፉባቸው ፓርኮችም ሆኑ ሌሎች መዳረሻዎች ባለመኖራቸው ቅሬታቸውን ይገልጹ ነበር። ይህ ሁኔታ አዲስ አበባን ለስራ እንጂ ለቱሪስት መስህብነትና መዝናኛነት እንዳትመረጥ አድርጓት እንደቆየ ተናግረዋል።
ወይዘሮ ሶስና በአሁኑ ወቅት በከተማዋ የተገነቡት አዳዲስና ዘመናዊ የመዝናኛ ስፍራዎች የጎብኝዎችን ጥያቄ በሚገባ የመለሱና ለውጭ እንግዶች መዳረሻ መሆናቸውን ያስረዳሉ። እነዚህ አዳዲስ መዳረሻዎች የከተማዋን ገጽታ ከመቀየር ባለፈ፣ የውጭ አገር ዜጎችም ሆኑ የአገር ውስጥ ጎብኝዎች ጊዜያቸውን በደስታ የሚያሳልፉባቸው አማራጮችን በስፋት ፈጥረዋል። በአጠቃላይ ባለፉት ዓመታት በመዲናዋ የተሰሩት ስራዎች በርካታ የውጭ የኪነ ጥበብ ሰዎችና ጎብኝዎችን ቀልብም ጭምር ለመሳብ ችለዋል፡፡
የመዲናዋ የጥበብ እንግዶችና ምስክርነታቸው
ባለፉት ስምንት ዓመታት የተከናወኑ ተግባራት ከተማዋን የአፍሪካ የዲፕሎማሲ መድረክ ብቻ ሳትሆን የጥበብና የውበት ማዕከል እንድትሆን አድርጓታል። ለኑሮ ምቹ ያልነበሩ የከተማዋ ስፍራዎች በአሁኑ ወቅት በዘመናዊ የመሠረተ ልማት ግንባታዎችና በፈጠራ ስራዎች እየተተኩ ይገኛሉ። ይህ ሽግግር የአገር ውስጥ ባለሙያዎችን ብቻ ሳይሆን በዓለም አቀፍ ደረጃ ስም ያላቸው የኪነ-ጥበብ ሰዎችን ትኩረት የሳበና ከተማዋን በአዲስ መነጽር እንዲመለከቷት ያስገደደ ትልቅ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።
መዲናዋን የጎበኙ የጥበብ ሰዎች በሰጡት ምስክርነት በዋናነት የሚጠቀሰው የአረንጓዴ ልማትና የፓርኮች ግንባታ የከተማዋን ድባብ ሙሉ በሙሉ መቀየሩን ነው። እንደ አንድነት እና እንጦጦ ፓርኮች፣ ወዳጅነት አደባባይ ያሉ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ ውበትን ያጣመሩ ፓርኮች ለከያንያኑ የፈጠራ መነሳሳትን የሚፈጥሩ ስፍራዎች ሆነዋል።
ከውበት ባሻገር፣ ከተማዋ ለዓለም አቀፍ የኪነ-ጥበብ መድረክነት ያላትን ብቃት በተግባር እያረጋገጠች ትገኛለች። በተለይ የዓድዋ ድል መታሰቢያ እና ዘመናዊው የቤተ-መጻህፍት ግንባታዎች የጥበብ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያ ታሪክና ስልጣኔ ያላቸውን ግንዛቤ ከፍ አድርጎታል። ይህም ዝነኛ ድምፃውያን፣ የፊልም ባለሙያዎችና ዲዛይነሮች ስለ ከተማዋ እድገትና ንጽህና በአድናቆት እንዲናገሩ በር ከፍቷል። ባለፉት ዓመታት አዲስ አበባን ደቡብ ሱዳናዊቷን አርቲስት ስላቲን ፕሮን እና ዓለም አቀፋዊው ይዘት ፈጣሪን አይሾው ስፒድን ጨምሮ በርካታ የጥበብ ሰዎች መዳረሻ መሆን ችላለች፡፡
ለአብነትም ስመጥሯ የማሊ ሙዚቀኛ ኡሙ ሳንጋሬ በአዲስ አበባ ያደረገችው ጉብኝት፣ የመዲናዋን አዲስ ገጽታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዳግም ያስተዋወቀ አጋጣሚ ነበር። ድምጻዊቷ በእንጦጦ ፓርክ፣ በሙዚየሞችና በተለያዩ የልማት ስፍራዎች ተገኝታ ባደረገችው ምልከታ እጅግ ተደስታለች። በተለይም በአጭር ጊዜ ውስጥ የተከናወነው የከተማዋ ለውጥ ከጠበቀችው በላይ ሆኖ እንዳገኘችው በመግለጽ፣ የአዲስ አበባን ፈጣን ሽግግርና ውበት በአድናቆት መስክራለች።
ኡሙ ሳንጋሬ የአዲስ አበባን ለውጥ የገለጸችው “በኒው ዮርክ ከተማ ያለሁ ያህል ተሰምቶኛል” በማለት ነበር፡፡ ይህ አስተያየቷ አዲስ አበባ የደረሰችበት የለውጥ ደረጃ፣ የመዝናኛ አማራጮች እና የአረንጓዴ ልማት ስራዎች ዓለም አቀፍ ደረጃን የጠበቁ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ ነው። እንዲህ ያሉ የኪነ-ጥበብ ሰዎች ምስክርነት ከተማዋ ለቱሪዝም ያላትን ተመራጭነት ከማሳደጉም በላይ፣ አዲስ አበባ የታሪክና የዘመናዊነት መገናኛ መሆኗን በተግባር የሚያሳይ ነው።
ከሰሞኑ ደግሞ ዝነኛው አሜሪካዊ የራፕ ሙዚቃ ኮከብና የዲጂታል ይዘት ፈጣሪ ዳሪል ድዌይን ግራንቤሪ (ዲዲጂ) አዲስ አበባን መጎብኘቱ ይታወቃል። ይህ ጉብኝትም ከተማዋ ለዓለም አቀፍ ዝነኞች ያላትን ሳቢነት ዳግም አረጋግጧል። አርቲስቱ በመዲናዋ እምብርት የሚገኘውን የዓድዋ ድል መታሰቢያን በጎበኘበት ወቅት፣ የጥቁር ሕዝቦች ኩራት በሆነው የዓድዋ ድል ታሪክና በጀግኖች አባቶች ገድል ዙሪያ ሰፊ ገለጻ ተደርጎለታል። ይህ ጉብኝቱ አዲስ አበባ የዘመናዊነት ብቻ ሳይሆን፣ ጥልቅ የታሪክና የማንነት መፍለቂያ መሆኗን ለተከታዮቹ ለማሳየት ትልቅ አጋጣሚ ፈጥሯል።
ዲዲጂ በመታሰቢያው ውስጥ የሚገኙ ታሪካዊ ቅርሶችን፣ የጀግኖችን ተጋድሎ የሚዘክሩ የጥበብ ስራዎችንና የድሉን ታላቅነት የሚያሳዩ ምስሎችን ተመልክቷል። አርቲስቱ በታሪካዊ ጉብኝቱ ብቻ ሳይወሰን፣ የኢትዮጵያን ባህላዊ የቡና ሥነ-ሥርዓት በሀገርኛ አቀራረብ በመታደም የሀገሪቱን ልዩ እንግዳ ተቀባይነት አድንቋል። ይህ በባህላዊ እሴቶችና በታሪክ የታጀበ ቆይታው፣ አዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻነቷን ከማሳደጉም ባለፈ የጥበብ ሰዎች የአፍሪካን ጥንካሬና ውበት የሚረዱባት ማዕከል መሆኗን አስመስክሯል።
የዲዲጂ እና የሌሎች አርቲስቶች ጉብኝት መዲናዋ ባለፉት ስምንት ዓመታት ያስመዘገበችውን የለውጥ ጉዞና የገነባቻቸውን ታላላቅ ፕሮጀክቶች ለዓለም የሚያስተዋውቅ ነው። ምክንያቱም እንደ ኡሙ ሳንጋሬ ሁሉ፣ ዲዲጂም በከተማዋ መሠረተ ልማትና በታሪካዊ ስፍራዎች አሰራር መገረሙ፣ አዲስ አበባ ለዓለም አቀፍ የጥበብ መድረክነት ያላትን ዝግጁነት ያሳያል። እንደነዚህ ያሉ የዝነኞች ጉብኝት ከተማዋ በመዝናኛ መዳረሻነት፣ በልማት፣ በውበትና በታሪክ እንድትታወቅ በማድረግ ረገድ የማይተካ ሚና ይጫወታሉ።
በአጠቃላይ፣ የአዲስ አበባ ያለፉት ዓመታት የለውጥ ጉዞ ለቱሪዝም ዘርፉ ከፍተኛ መነቃቃትን ከመፍጠሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ የጥበብ መድረክ ላይ ያላትን ተጽዕኖ እያሳደገው ነው። ከተማዋ እያስመዘገበች ያለው እድገት በኪነ-ጥበብ ሰዎች እይታ፣ አዲስ አበባ የጥንታዊነትና የዘመናዊነት ስምምነት የሚንጸባረቅባት፣ ለፈጠራ ስራዎች ምቹና ለጎብኚዎች ማራኪ መሆኗን ያሳያል። ይህ ደግሞ መዲናዋ ወደፊትም የጥበብና የባህል አምባ ሆና እንድትቀጥል የሚያደርጋት ትልቅ መሠረት ነው።