AMN- መጋቢት 28/2018 ዓ.ም
አሜሪካ እና ኢራን በዛሬው ዕለት ሥራ ላይ ሊውል የሚችልና የሆርሙዝ ሰርጥን በድጋሚ የሚያስከፍት የሰላም እቅድ እንደደረሳቸው ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ምንጮች መግለፃቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
በፓኪስታን የተዘጋጀውና ግጭቱን ለማቆም የሚያስችለው ይህ ረቂቅ ሰነድ፣ ትላንት ሌሊቱን ለኢራንና ለአሜሪካ የቀረበ ሲሆን፣ ሂደቱም በሁለት ደረጃዎች የሚከናወን ነው።
የመጀመሪያው ደረጃ አፋጣኝ የተኩስ አቁም ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ሁሉን አቀፍ ስምምነት ላይ መድረስ መሆኑ ተገልጿል።
አክሲዮስ የተሰኘው የዜና ምንጭ ባሳለፍነው እሁድ እንደዘገበው፤ አሜሪካ፣ ኢራን እና ቀጣናዊ አሸማጋዮች ለ45 ቀናት የሚቆይ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ እየተወያዩ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ይህም ለዘላቂ ሰላም መንገድ እንደሚከፍት የአሜሪካ፣ የእስራኤል እና የቀጣናው ምንጮችን በመጥቀስ ምንጩ ዘግቧል።
የሮይተርስ ምንጮች እንደገለጹት፤ የፓኪስታን ጦር አዛዥ ፊልድ ማርሻል አሲም ሙኒር ከአሜሪካው ምክትል ፕሬዚዳንት ጄዲ ቫንስ፣ ልዩ መልዕክተኛ ስቲቭ ዊትኮፍ እና ከኢራኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራቅቺ ጋር ሌሊቱን ሙሉ ሲመክሩ አድረዋል።
“የኢስላማባድ ስምምነት” ተብሎ በጊዜያዊነት በተሰየመው በዚህ የሰላም እቅድ መሰረት፦ የተኩስ አቁሙ በአስቸኳይ ሥራ ላይ ይውላል፣ የሆርሙዝ ሰርጥ ወዲያውኑ ለትራንስፖርት ክፍት ይሆናል፣ በቀጣዮቹ ከ15 እስከ 20 ቀናት ውስጥ ዘላቂ ሰላምን የሚያሰፍን ስምምነት ይፈረማል።
የመጨረሻው የገፅ ለገፅ ንግግርም በፓኪስታን መዲና ኢስላማባድ የሚካሄድ ይሆናል።
በታምራት ቢሻው