AMN መጋቢት 30/2018 ዓ.ም
የኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ መሀመድ፣ በጃፓኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ልዩ አማካሪ ኦዌ ሳዳማሳ የተመራውን የልዑካን ቡድን በፅህፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
በቆይታቸውም የሁለቱን አገራት ብሄራዊ ጥቅም፣ የጋራ ፍላጎትና እሴቶችን ባከበሩ የፀጥታ ጉዳዮች ላይ በቅንጅት መስራት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ዙሪያ ሰፊ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ ወቅት ልዩ አማካሪው ኦዩኢ ሳድማሳ፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካም ሆነ በአህጉር ደረጃ ሰላምና መረጋጋትን ለማስፈን የምታከናውናቸውን ተግባራት አድንቀዋል።
በተለይም አገሪቱ በሰላም ማስከበር ረገድ ያላትን ሰፊ ተሞክሮ ከግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጃፓን በዚህ ዘርፍ ከኢትዮጵያ ጋር ተቀራርቦ ለመስራት ያላትን ከፍተኛ ፍላጎት አረጋግጠዋል።
ጃፓን የኢትዮጵያን የሰላም ማስከበር ማዕከል አቅም ለመገንባት ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን የጠቆሙት አማካሪው፤ በስልጠና እና በልምድ ልውውጥ የመከላከያ ሰራዊቱን የሰው ኃይል የሙያ ብቃት ለማሳደግ ያላቸውን ቁርጠኝነት አሳይተዋል።
ክብርት ኢንጂነር አይሻ በበኩላቸው፣ ጃፓን ለትብብር ያሳየችውን ተነሳሽነት በማድነቅ፤ ኢትዮጵያ በእውነተኛ ወዳጅነትና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሰረተ ጠንካራ ወታደራዊ አጋርነትን ለማጠናከር ዝግጁ መሆኗን አመልክተዋል። ይህ ትብብር በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን የቆየ ወዳጅነት ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያሸጋግረውም ያላቸውን እምነት ገልፀዋል። ዘገባውን ያደረሰን የመከላከያ ኦንላይን ሚዲያ ነው።