“ምክክር ከሕማም እና ከጨለማየምንሻገርበት ትንሣኤ ነው”

You are currently viewing “ምክክር ከሕማም እና ከጨለማየምንሻገርበት ትንሣኤ ነው”

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)

ክረምት የመብረቅና የነጎድጓድ ድምፅ በብዛት የሚሰማበት፤ የባሕርና የወንዞች ሙላት የሚያይልበት፤ ሰማይ ደመናን እንደ ጋቢ ተከናንቦ ፀሐይን የሚጋርድበት ወቅት ነው። ሀገርም አንዳንዴ ዘመኗ እንዳይገለጥ እንደ መብረቅና ነጎድጓድ የሚያስደነግጡ እና የትንሣኤዋ ብርሃን እንዳይታይ በከፍታዎቿ ዙሪያ እንደ ጉምና ጭጋግ ሆነው የሚጋርዱ ብዙ ፈተናዎች አሉባት።

ደራሲ ሊዮ ቶልስቶይ በበርካቶች ዘንድ የሥነ ምግባር ፈላስፋ፣ ማኅበራዊ ሕጸጾችን ተቺ እና የሰው ልጆች የሕሊና ድምፅ በመባል ይታወቃል። የዚህ ሩሲያዊ ደራሲ የመጨረሻ እንደሆነች የሚነገርላት ‘ትንሣኤ’ የተሰኘችው መጽሐፉ እ.ኤ.አ በ1899 ዓ.ም ለሕትመት በቅታለች።

ሊዮ ቶልስቶይ በዚህ መጽሐፉ እንደገለጸው፣ ከኃይማኖቱ አስተምህሮ ባሻገር እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ማኅበረሰብ በሙሉ ሞራልና መንፈሳዊ ኃይል ዳግም መወለድ ነው ትንሣኤ። እንደ ክረምት መብረቅና ነጎድጓድ፣ የወንዝ ሙላትና መሻገሪያ ማጣትን የመሳሰሉ ከባባድ ችግሮች ባሉበት ወቅት በልቦናና በሕሊና ትንሣኤ ዳግም መወለድን እና ካሰቡት መድረስን ያህል ምን የሚያስደስት ነገር አለ? ይለናል።

ትንሣኤ መታደስን፣ ፍትሕን እና ተስፋን ያመለክታል። ታዲያ ከትንሣኤ በፊት የሰው ልጅ አሊያም አንድ ሀገር በድህነት፣ በኢፍትሐዊነት ወይም በችግር ብዙ የሕማማት ወቅቶችን ሊያሳልፍ ይችላል።

ወዲህ ደግሞ እርስ በእርስ መደጋገፍ፣ መመካከር እና አንዱ ለአንዱ ከፍታ ከፊት መቆም ከቻለ የሀገር ትንሣኤ ሩቅ አይሆንም። እውነተኛ ብሔራዊ እድገት የሚጀምረው በግለሰብ የሕሊና ትንሣኤ ነውና። የእያንዳንዳችን የሕሊና ትንሣኤ ሲደመር የማኅበረሰብ ትንሣኤ ይሆናል። ተፈጥሮ ከክረምት ወደ ጸደይ እንደምትሸጋገር ሁሉ፣ ማኅበረሰብም ችግርን በምክክር ሲፈታ ሀገራዊ ትንሣኤው እውን እንደሚሆን ሊዮ ቶልስቶይ በልብ ወለድ ድርሰቱ አስታኮ የገሀዱን ዓለም ሀቅ ይነግረናል።

ኢትዮጵያም፣ በሰለጠነ መንገድ ሊፈቱ የሚችሉ ችግሮች ጥርስ እያስነከሱ፣ እያመረቀዙ፣ ጦር እያማዘዙ፣ ቂም እያስረገዙ ድንገት እንደ በረዶ በሚወርዱ መከራዎች እየተመታች ቀንና ሌሊቷ ተጨፍኖ ብዙ ክረምቶችን አሳልፋለች።

ረሃብ፣ ጦርነት እና ስንፍናን የመሳሰሉ ክረምቶች በኢትዮጵያ ምድር የትንሣኤዋን ብርሃን ጋርደው ለዘመናት አልፈዋል። እናም ሀገር ትንሣኤ ትሻለች። ፋሲካዋ አሊያም መሸጋገሪያዋ ደግሞ ሁላችንንም ሰቅዘው የያዙ እና ጦር የሚያማዝዙ ችግሮችን በሰለጠነ መንገድ መፍታት የሚያስችለው ሀገራዊ ምክክር ነው።

“ከምንም በላይ ድህነት መራር ነው፤ የኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን የአስተሳሰብ ድህነትም ይዞት የሚመጣው ዳፋ ብዙ ነው” የሚሉት የሥነ ልቦና ባለሙያውና አማካሪ አቶ ማኅደር ሳልህ፣ በድህነታችን ቀዳዳ ታሪካዊ ጠላቶቻችን እየገቡ እርስ በእርስ አናክሰውናል፣ በስንፍናችን ላይ ሌሎች ሸክሞችንም ጨምረውብናል። ወደ ስልጣኔ ጎዳና እንዳንሻገር እንቅፋት ሆነውብናል። ከዚህ ለመውጣት ደግሞ አለመግባባቶቻችንን በሀገራዊ ምክክር ፈትተን ለሀገር ትንሣኤ በጋራ መቆምና መሥራት አለብን ብለዋል።

ሀገርን ከጥልቅ እንቅልፍ የሚያነቃ ነው የሀገራዊ ምክክር። በመመካከር ችግርን መሻገር፣ የጋራ ከፍታን መጨመር እና ከሥልጣኔ ጋር መወዳጀት ብሎም የሀገርን ትንሣኤ ማብሰር ነው የሀገራዊ ምክክር ዋና ዓላማው።

ታዲያ ትንሣኤ በቀላሉ የሚገኝ አይደለም የሚሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የኃይማኖት መምህሩ መጋቢ ሐዲስ እረጌ አየለ፣ ይልቁንም የክርስቶስ ትንሣኤ ከድል በፊት ያለውን አስቸጋሪ ጉዞን ያመለክታል። ይኸውም ትንሣኤ በመከራ፣ በጽናት እና በመጨረሻም በድል የሚጠናቀቅ ጣፋጭ ገድል ነው። በኃይማኖታዊ አስተምህሮ ትንሣኤ በነጻ የሚሰጥ አይደለም፤ በፈተናዎች የሚገኝ እንጂ። በመሆኑም ኃይማኖታዊው የትንሣኤ አስተምህሮ ለነፍሳችን መታደስና ከፍታ ትልቅ ዋጋ እንዳለው ሁሉ ለሀገራችንም ትንሣኤ ሁላችንም ችግሮቻችንን በምክክር በመፍታት፣ ይቅር በመባባል፣ አንዳችን ለሌላችን መዳን ልንኖር ይገባል ብለዋል።

የሥነ ልቦና ባለሙያና አማካሪ አቶ ማኅደር ሳልህ በበኩላቸው፣ በተመሳሳይ መንገድ ብሔራዊ ምክክር የፖለቲካ ልምምድ ብቻ ሳይሆን፣ መከራን የመጋፈጥ፣ ከእሱ የመማር እና ወደ ዘላቂ መፍትሔዎች የመቀየር የጋራ ሂደት ነው።

በዚህ መነጽር ሲታይ፣ ምክክር የማኅበራዊ ትንሣኤ ወሳኝ ምዕራፍ ነው። ይኸውም ለዘመናት እንቅፋት የሆኑ ችግሮቻችንን የምንቀርፍበት፣ በአዲስ አስተሳሰብና ከፍታ ታላቅነታችንን የምናበስርበት፣ በጋራ ጽናት የሚገኝ እና ዳግም ሀገር የምትወለድበት እንዲሁም በአዲስ አስተሳሰብና ልዕልና የምትነሣበት ትልቅ ዕድል ነው ሀገራዊ ምክክር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ መምህር ሰሎሞን ተክሌ እንደሚሉት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ አስተምህሮ የትንሣኤ ዓይነቶች አምስት ናቸው። እነሱም የክርስቶስ ትንሣኤ፣ ጊዜያዊ ትንሣኤ፣ ትንሣኤ ዘጉባኤ፣ ትንሣኤ ዘልቦና እና ትንሣኤ ዘሕሊና ናቸው። ከእነዚህ ውስጥ ደግሞ በሕሊና ትንሣኤ የታሰበው በልቦና ትንሣኤ ተግባራዊ ይደረጋል። በሕሊና ትንሣኤ ንስሐ ለመግባት ያሰበ ሰው በልቦና ትንሣኤ ንስሐ ይገባል። በአጠቃላይ መንፈሳውያን መልካምነትን ወደ ተግባር የሚቀይሩበት ሕይወት ነው የሕሊና ትንሣኤ።

ኃይማኖታዊ ትርጓሜው እንደተጠበቀ ሆኖ እያንዳንዳችን በሕሊናም በልቦናም ልንነሣ ይገባል። ይህ ሲሆን የነፍስ ትንሣኤ ለሥጋም ይተርፋልና የሀገርም ትንሣኤ እውን ይሆን ዘንድ ችግሮቻችንን በይቅርታና በምክክር መፍታት ይኖርብናል ብለዋል።

በዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት መምህር ሙሉጌታ አስፋው ከግለኝነት ወይም እያንዳንዱ ራሱን፣ ማንነትና ፍላጎቱን ከሚያንጸባርቅበት ወደ ጋራ ማንነት መምጣት የሚቻለው ነገሮችን በጠረጴዛ ዙሪያ አምጥቶ በመነጋገር ነው። በዚህም የነበሩንን ጠንካራ ጎኖች ወይም አንድነትና ሕብረትን የሚያጸኑ ጉዳዮችን ማጎልበትና ማጠናከር ያስፈልጋል። ሀገራዊ ምክክሩም ይህንን የሚያግዝ ነው ብለዋል።

እንደ ሀገር የነበረን የአንድነት ስሜት እንዲሸረሸር እና ግለኝነት የበላይ እንዲሆን ያደረገው ብዙ ነገር ቢሆንም፣ በተለያዩ ጊዜያት የነበሩና ያሉ የፖለቲካ ልሂቃን የተለያዩ መድረኮችን እና መገናኛ ብዙኃንን በመጠቀም የግል አጀንዳቸውን በማራመድ በመሥራታቸው ጭምር የመጣ ነው። በመሆኑም የጋራ የሆነውን ነገር ማምጣት የምንችለው ክፍተቶቻችን ላይ ሁሉም የሚመለከተው አካል እንዲነጋገርበት ሲደረግ እንደሆነም ተናግረዋል።

ለዚህ ደግሞ ሀገራዊ ምክክሩ ብሔራዊነትን ለመገንባት የሚኖረው ፋይዳ ትልቅ ነው። ለዚህም እነ ሩዋንዳን የመሳሰሉ የአፍሪካ ሀገራት ተምሳሌቶች ናቸው ብለዋል የፖለቲካ ሳይንስ ምሁሩ አቶ ሙሉጌታ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር) ከዝግጅት ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፣ የኢትዮጵያ ትንሣኤ ወይም ድል በዋናነት አንዳችን ሌላችንን ስናከብር፣ ስንተዛዘን፣ ስንደማመጥና ስንመካከር የሚመጣ ነው። የነበሩ ቁስሎቻችንን ማከም የምንችለው ካለፈው ትምህርት በመውሰድና ይቅር በመባባል ነው። ሀገራዊ ምክክሩ አንዳችን ሌላ ቦታ ሆነን ችግሩን በመረዳት፣ ቁርሾዎችን ከውስጥ በማውጣት፣ ይቅር በመባባል፣ ዳግም ወደኋላ ላለመመለስ ቃል በመግባት ራሳችንን የምናድስበት ነው።

ታዲያ ድርድርና ሽምግልና የመሳሰሉት የአጭር ጊዜ መፍትሔ ናቸው። ምክክር ግን ረጅም ጊዜ እና በተለይም ለዘመናት የቆዩ ችግሮቻችንን ለመፍታት ግንባር ቀደም ሚና ይጫወታል። በምክክር ብዙ ነገሮች አሉ የሚሉት ኮሚሽነር ዮናስ (ዶ/ር) ለአብነትም ውይይት፣ ምክር እና ጭውውትን መጥቀስ እንችላለን። ውይይት ወደኋላ ተመልሰን ችግሮቻችንን የምናይበት መነጽር ነው። ምክር ደግሞ ካለፈው በመማር ወደፊት እንዴት እናድርግ በማለት ሰዎች ወደፊት የሚያዩበት ነው። ሦስተኛው ደግሞ ሰዎችን እንደ ድልድይ የሚያገናኛቸው ጭውውት ነው። ይህም ሰዎች ልምዳቸውን፣ ተስፋቸውን እና ስጋታቸውን በዝርዝር የሚነጋገሩበት ነው። በመሆኑም እነዚህን ድንቅ ሐሳቦች የያዘው ምክክር ነው።

በመሆኑም ምክክር ነገሮችን ከሥር መሠረቱ በማየት፣ ሰዎች ሌላውን ሐሳብ ሳይቃወሙ እና ሳይንቁ፣ በመተባበርና በመደማመጥ አንዳችን የሌላውን ቁስል ለመፈወስ የምንዘጋጅበት የፈውስ እና የእውነት ፍለጋ ሂደት ነው። ይህም ፈውስ ለሀገር ትንሣኤ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል።

ከዚህ በፊት የነበሩትን ችግሮች በሚገባ በመፈተሽ በጥልቀትና አንዱ ሌላውን አክብሮና ሳይፈራ በሽታውን የሚያወጣበት ሂደት ነው። በመሆኑም ምክክር ለሀገር ፈውስ ነው። ከጨለማ ወደ ብርሃን የሚወስደንም መንገድ ነው ብለዋል።

ትንሣኤ እንደ በዓል የሚከበረው እሑድ ነው። ግን እሑድ ለመድረስ ስቅለት ያስፈልጋል። በመሆኑም መከራው እና ጨለማው አርብና ቅዳሜ ላይ ያለው ነው። ስለዚህም የምክክሩ ትንሣኤ እሑዱ ነው። በመሆኑም የሀገር ትንሣኤ ቀደም ሲል የነበሩትን ለምሳሌ ስቅለቱን፣ መቃብሩን እና ጨለማውን አልፎ የሚመጣ ነው። በመሆኑም “ምክክር ከሕማማት፣ ከቁስለት፣ ከጨለማ ወደ ብርሃን የምንሸጋገርበት ትንሣኤ ነው” ይላሉ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ (ዶ/ር)።

ሰሞነ ሕማማትን ስናስብ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበሩ ጭንቀቶችን፣ የእርስ በእርስ መገፋፋትን እና መሰል ችግሮቻችንን እንመለከታለን። በመሆኑም የሁላችን ቁስል ማከሚያ መንገዱ ምክክር ነው። ስለዚህ ምክክር የሀገር ትንሣኤ ነው። እንደ ኃይማኖት አስተምህሮ “ክርስቶስ ተነሣ” ብለን መልካም ነገሮቻችንን እንደማናቆም ሁሉ፣ ሕይወት እስካለ ድረስ መከራ ስላለ እንኳን ለወገናችን ቀርቶ ለሚጠሉን ሁሉ ዘወትር ፍቅርን በማሳየት ምክክር ባህላችን ሆኖ መቀጠል አለበትም ብለዋል።

ዜያትም እየተከናወነ ይገኛል። ይህም የከተማ አስተዳደሩ ለማኅበረሰቡ ያለውን ተቆርቋሪነትና የመረዳዳት እሴታችንን የማጎልበት ቁርጠኝነት ያሳያል። የማዕድ ማጋራት ፕሮግራሞች አቅመ ደካሞችንና የሀገር ባለውለታዎችን ከመርዳት ባለፈ፣ የማኅበረሰቡን አንድነትና ፍቅር የሚያጠናክሩ ናቸው። በተለይም በመጪው የትንሣኤ በዓል፣ በችግር ውስጥ ያሉ ጎረቤቶችንና ሌሎችንም መደገፍና ደስተኛ ሆነው በዓሉን እንዲያሳልፉ ማድረግ ከከተማ አስተዳደሩ ባለፈ ከእያንዳንዱ ማኅበረሰብ አባል ይጠበቃል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ የትንሣኤ በዓልን ምክንያት በማድረግ፤ ለማኅበራዊ ችግር ለተጋለጡ፣ ለአካል ጉዳተኞች፣ ጧሪና ደጋፊ ለሌላቸው የሀገር ባለውለታ አረጋውያንና በዝቅተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ የመንግስት ሰራተኞች በአጠቃላይ ከ233 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ወገኖች ማዕድ ማጋራታቸውም የዚሁ የመረዳዳት ቱባ ባህል አካል ነው፡፡

ማዕድ የማጋራቱ ተግባር በከተማዋ የማዕከል መስሪያ ቤቶች፣ በሁሉም ክፍለ ከተሞችና ወረዳዎች ጭምር ተከናውኗል፤ ይህንኑ አስመልክቶ ከንቲባ ወይዘሮ አዳነች፣ “በሁሉም በዓላት የምናደርገው የማዕድ ማጋራት፣ ድጋፍ የሚሹ የከተማችን ነዋሪዎችን ‘ምን ጎደለ?’ ብለን በመመልከትና በመጠየቅ ክፍተታቸውን የምንሞላበት፣ ለነዋሪዎቻችን ያለንን ክብር የገለፅንበት ሰው ተኮር ተግባር ነው” ማለታቸው ይታወሳል፡፡

የኢትዮጵያውያን የእርስ በርስ የመረዳዳትና የመደጋገፍ እሴታችን በትንሣኤ በዓል ወቅት ይበልጥ ጎልቶ መታየት አለበት። በችግር ውስጥ ያሉትን መርዳት፣ ደስታን የጋራ ማድረጊያ መንገድ ነው። በመሆኑም፣ እያንዳንዱ ማኅበረሰብ በመጪው የትንሣኤ በዓል፣ በችግር ውስጥ ያሉትን መርዳትና ደስተኛ ሆነው በዓሉን እንዲያሳልፉ ማድረግ አለበት። ይህ ተግባር የማኅበረሰቡን አንድነትና ፍቅር የሚያጠናክር ከመሆኑ ባለፈ፣ የሀገራችንን ብልጽግናና ሰላም ለማረጋገጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል። እርስ በርስ የመረዳዳት እሴታችንን ይበልጥ እናጎልብተው!

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review