AMN – ሚያዝያ 5/2018 ዓ.ም
የትንሳኤ በዓል በመላው ዓለም የሚገኙ የክርስትና እምነት ተከታዮች የኢየሱስ ክርስቶስ ሞትን ድል አደርጎ መነሳትን በማሰብ በልዩ ልዩ መንፈሳዊ ሥርዓቶች በታላቅ ድምቀት የሚከበር በዓል ነው።
ኢትዮጵያ፣ በሩሲያ: በኢየሩሳሌም፣ በዩክሬይን፣ በቤላሩስ፣ በግሪክ፣ በሜቄዶንያ፣ በሞሎዶቪያ፣ እንግሊዝ፣ በጀርመን፣ በፈረንሳይ፣ በጣሊያን ሮም እና ስፔን በዓሉ በድምቀት ከሚከበርባቸው ሀገራት መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
የትንሳኤ ወይንም ፋሲካ በኢትዮጵያ በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ፣ በካቶሊክ እና በወንጌላውያን አብያተ ክርስቲያናት በጸሎት፣ በስግደት፣ በኃይማኖታዊና ክዋኔዎች ተከብሯል፡፡
እንዲሁም ጾሙ ሲፈታ፣ በቤተሰብ ተሰብስቦ ዶሮ ወጥ፣ ስጋ እና ሌሎች የፍስክ ምግቦችን በመመገብ እና ማዕድ በማጋራት ይከበራል፡፡
ኢየሩሳሌም የክርስቶስ ስቅለትና ትንሳኤ የተፈጸመባት በመሆኗ፣ በዓሉ በመላው ዓለም ካሉ ክርስቲያኖች ጋር በልዩ ድምቀት ይከበራል።
በብራዚል የትንሳዔ ዕለትን ምዕመናን አበባዎችን በየቤተ ክርስቲያኑ ይዘው በመሄድ ከንስሃ አባቶቻቸው ዘንድ ልዩ ቡራኬን ይቀበላሉ።
ሜክሲኮዎች በበዓሉ ዋዜማም ልክ እንደ ደመራ በወረቀት የተሰሩ ምስሎችን በሕዝብ ፊት የማቃጠል ሥነ-ሥርዓት ያከናውናሉ።
ጀርመኖች ደግሞ በዓሉን የሚያደምቁና ለልጆች ስጦታ የሚያድሉ ‘ኢስተርን በኒ’ ወይም የፋሲካ ጥንቸሎችም አንዱ የአከባበሩ ማድመቂያዎቻቸው ናቸው።
የትንሳዔ በዓል በሩሲያ ከበዓሉ በፊት ባሉት ቀናት በአብያተ ክርስቲያናት ዙሪያ ኃይማኖታዊ ሰልፎችን በማዘጋጀት ሲነጋ ጎረቤቶችን ከመጎብኘት እና የትንሳኤ እንቁላሎችን ከመስጠት ይጀምራል።

በዕለቱም “ክርስቶስ ተነሥቷል!”፤ “በእውነት ተነሥቷል!” የሚሉትን ድምጾች በማሰማት ሲሆን ይህን ተክትሎ በባህላዊ ሰላምታ በመለዋወጥ በዓሉ አክብረዋል፡፡
ክርስቶስ 40 ቀናት በጾም በጸሎት ማሳለፉን ለማሰብ በሰሞነ ህማማት ከረቡዕ ጀምሮ እስከ ትንሳዔ ፈረንሳዊያን በጾም በጸሎት ነው የሚያሳልፉት።
በፈረንሳይ ያለው የትንሳዔ በዓል አከባበር ስርዓት ከሌሎች የምእራባዊያን ሀገራት ጋር ተመሳሳይነት እንዳለው ነው የሚነገረው፡፡
በስፔን በትንሳዔ ዕለት የንስሃ አባት ለንስሃ ልጆቻቸው የኬክ ስጦታ ያበረክታሉ። በትንሳኤ ጊዜ የእንቁላል ምግቦችም ይዘጋጃሉ፡፡
በወተት፣ በእንቁላልና በስኳር ርሶ በዘይት የተጠበሰ ዳቦም ይዘጋጃል። ይህ ዳቦ ደግሞ ከማር፣ ከስኳርና ከሌሎች ጣፋጮች ጋር ለገበታ የሚቀርብ ሲሆን፣ የወይን መጠጦችም በማባያነት ይዘጋጃሉ።
በጣሊያን ለትንሳዔ በንስሃ መንጻት አንዱ ሃይማኖታዊ ግዴታ ሲሆን በአቢያተ ክርስቲያናት የሚካሄደው ስነ ስርዓትም የጣሊያኖች የፋሲካ አከባበር አንድ አካል ነው፡፡ የሃይማኖት አባቶች ለምዕመናን ቡራኬ ይሰጣሉ።
በቫቲካን ቅዱስ ጴጥሮስ ካቴድራል በሊቀ ጳጳሱ የሚሰጠው የትንሳኤ ቡራኬ እጅግ በርካታ ምዕመናን የሚታደሙበት ደማቅ ስነ-ስርዓት ነው፡፡
በተለይም በዕለተ አርብ በሮማ አደባባይ ሚያሸበርቁ መብራቶች ደምቆ የሚታየው መስቀል፣ የክርስቶስን ስቅለት በመዘከር የጸሎት ስነ-ስርዓቱ መጀመሩን ያበስራል።
በወርቅነህ አቢዮ