AMN- ሚያዝያ 6/2018 ዓ.ም
በመካከለኛዉ ምስራቅ ከተከሰተዉ እና እስካሁን ድረስ ዘላቂ መፍትሄ ካልተገኘለት የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ በርካታ የአለም ሃገራት በነዳጅ አቅርቦትና ዋጋ መናር እየተፈተኑ ይገኛሉ፡፡
ሃገራቱ ይህንን አለም አቀፍ ተጽእኖ ለመቋቋም ነዳጅን በቁጠባ ከመጠቀም ጀምሮ የተለያዩ የመፍትሄ አማራጮችን በመተግበር ላይ ይገኛሉ፡፡
ሃገራችን ኢትዮጵያም የነዳጅ አቅርቦት ተጽእኖዉን ለመቀነስ የተለያዩ የመፍትሔ አማራጮችን በመተግበር ላይ የምትገኝ ሲሆን ህብረተሰቡም ለተግባራዊነቱ የበኩሉን ድርሻ በመወጣት ላይ ይገኛል፡፡
ይህንኑ የነዳጅ አቅርቦት ችግርን አስመልክቶ ኤኤምኤን ያነጋገራቸዉ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችም ችግሩ በዘላቂነት እስከሚፈታ ድረስ አጫጭር መንገዶችን በእግር ወይም በብስክሌት በመጓዝ ጠቃሚ እንደሆነ መክረዋል፡፡

የእግርና የብስክሌት ጉዞ ማድረግ ከነዳጅ ቁጠባ ባለፈ ለጤና እና ለትራፊክ መጨናነቅ መቀነስ ትልቅ ፋይዳ አለዉ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የኮሪደር እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ስራዎች ለብስክሌትና ለእግር ጉዞ አዳዲስ አማራጮችን ፈጥረዋል ብለዋል።
መኪና ያላቸው ግለሰቦች በእግር ለሚጓዙ መንገደኞች የትራንስፖርት ትብብር ሊያደርጉ እንደሚገባም አስተያየት ሰጪዎቹ አክለው ተናግረዋል፡፡

በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ ያለዉን የነዳጅ ስርጭት በቅርበት የሚከታተሉ የፖሊስ አባላትም መንግስት ያወጣዉ መመሪያ በአግባቡ በመተግባር ላይ መሆኑን በመቆጣጥና ህገ ወጥ ድርጊቶችን በመካለከል ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል፡፡
የመዲናዋ ነዋሪች እንደተናገሩት ከሆነ በነዳጅ ማደያዎች አካባቢ የሚታየውን የነዳጅ ስርጭት ይበልጥ በመከታተልና ህገወጥ አሰራሮችን በመቅረፍ የወጣዉን መመሪያ በአግባቡ መተግበር ያስፈልጋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ