“የባህር በር አልባነት፣ ገመናአልባነት ነው”

You are currently viewing “የባህር በር አልባነት፣ ገመናአልባነት ነው”

                       ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

አለማየሁ ማሞ (ሊዲንግ ሲማን) “ጥቂቶቹ …የኢትዮጵያ ባሕር ኃይል አባላት አስደናቂ ግለ – ታሪኮች” በሚል ርዕስ እ.ኤ.አ 2022 ባሳተሙት መፅሐፍ እንዲህ የሚል እውነት አለ፡፡ “አዎን ኢትዮጵያ በንጉሥ ኃይለሥላሴ ዘመን በ1948 ዓመተ ምህረት የተቋቋመና እስከ ደርግ ማብቂያ የቆየ የባሕር ኃይል ነበራት፡፡ ከራስ ካሳ እስከ ራስ ዱሜራ ያለውን ክልል በልሕቀት ያስከበረ ቆፍጣና የባሕር ኃይል ነበራት” በእርግጥም አሁን ነበር እራሱ ነበር ሆኗል፡፡ ምክንያቱም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ እንደ አዲስ ተቋቁሟልና፡፡

ኢትዮጵያውያኑ  የባሕር ኃይል አባላት

 “…የእምዬ ኢትዮጵያ መከታ ጋሻዎ፣

ጀግናው መርከበኛ የማህጸን ፍሬዎ፡፡” እያሉ ያዜሙት ‘መልህቅ አርማዬ’ የሚለው  መዝሙር በብዙዎቻችን ልቦና ሁሌም ነግሶ ይኖራል፡፡ አዎ ኢትዮጵያ የባህር በር ነበራት፤ የጥንታዊቷ ኢትዮጵያ የጂኦ-ፖለቲካ፣ የጂኦ-ኢኮኖሚክስ ድልና ከፍታን ከባሕር በር ለመለካት ብንሞከር ተመኑ በእርግጥም ህልቆ መሳፍርት ነው።

በታሪክ መስመር ላይ የኢትዮጵያ ምጥቀት ከፑንት እስከ ዳዕማትና አክሱማዊት መንግሥት ደግሞም እስከ ትላንት ትዝታችን እስከ ነገም ተስፋና ስኬታችን ወዲያና ወዲህ በዕውነት መነፅር ስንመለከት በእርግጥም የባህር በር ነበረን፤ አሁንም በፍትሕና  ርትዕ ሚዛን ሲለካ ይገባናል፡፡

“ባሕር እና ሥልጣ፤ የዓለም የባህር ታሪክ” (The Sea and Civilization A Maritime History of the World) በሚል እርዕስ እ.ኤ.አ ሰኔ 2015 ሊንከን ፔይን ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው የባሕር በር ለሀገራት ለምግብና መጓጓዣ ብቻ ሳይሆን የንግድ መስመሮችን፣ የኃይል አቅርቦትን አልፎ ተርፎም የመከላከያ አቅምን ማጠናከሪያ ማማ፣ ክንድን ማፈርጠሚያ ሰገነት ሆኖ በማገልገል የሀገራት ከፍታ መለኪያ እስከመሆንም ደርሷል፡፡

እናም በብዙ መለኪያዎች የኢትዮጵያ የባሕር በር በእጅጉ ያስፈልጋታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ባሳለፍነው ረቡዕ ሚያዝያ 7 ቀን 2018 ዓ.ም “የሉዓላዊነት ልብ” በሚል ርዕሰ ጉዳይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ከኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረጉት ቆይታ ያነሷቸውን ሀሳቦች መጥቀስ ነገሩን ምልዑ ያደርገዋል፡፡

በወቅቱም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የባሕር በር ለኢትዮጵያ ብልጽግና እና ህልውና ያለውን ቁልፍ ሚና እንዳለው ገልፀዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ፣ ዜጎቿን በበቂ መግባ ራሷን ችላ በዓለም ተወዳድራ የላቀች ሀገር ለመሆን ካሉባት ዋንኛ ማነቆዎች ትልቁ ችግር ባሕር አልባነት መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

የባሕር በር አልባነት የዲጅታል ገበያ አልባነት፣ የገቢ ወጭ ንግድ አልባነት  በአጠቃላይ ገበና አልባነት መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ምኒስትሩ፣ የባሕር በር አልባነት የሀገር ምስጢሮች አልባነት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡

የባሕር በር ጉዳይ ከዚህ ቀደም ሲነገር ከነበረው በተገለጠ እና በሚታይ መንገድ አሁን ባለው ሁኔታ ምን ያህል ጫና እና ችግር እንዳለው ሁሉም ሰው እያየው መሆኑን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ኢትዮጵያን የሚያክል ሀገር ከባሕር በር ርቃ መኖር የህልውና ጉዳይ መሆኑን ማንም ሰው በቀላሉ እንደሚገነዘበውም አብራርተዋል፡፡ ይህም ችግር በኢትዮጵያ ብልጽግና ላይ ከፍተኛ ማነቆ ሆኖ የሚቀጥልና ትውልድን የሚሻገር አጀንዳ መሆኑንም በአፅንኦት ተናግረዋል፡፡

የባሕር በር አልባነት በእያንዳንዱ ዜጋ ህይወት ላይ ተጽእኖ እያሳደረ እንደሚገኝም የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንንም በቀላሉ በንግድ ህግ፣ በንግግር እና በሰጥቶ መቀበል መርህ ማግኘት ሲቻል ከምጽዋ ጫፍ እስከ ሞቃዲሾ ቀንድ ድረስ ባለው 5 ሺህ ኪሎ ሜትር እጅግ በርካታ ሀብት ባለበት ቦታ ላይ በክፋት ባለመነጋገር፣ በሰጥቶ መቀበል መርህ ባለማመንና በጋራ ለመኖር ባለመዘጋጀት ኢትዮጵያን ወደብ አልባ አድርጎ መቀጠል በየትኛውም ዘመን አዋጪ እንዳልሆነ አሳማኝ አስረጅዎችን ጠቅሰው አብራርተዋል፡፡

ይህ ሁኔታ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ከባድ መሆኑን ያብራሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ተነጋግሮና ተመካክሮ ሁሉን አሸናፊ በሚያደርግ መንገድ መፍታት ካልተቻለ ችግሩ አሁን እንደሚታየው ሆኖ እንደሚቀጥል አሳስበዋል።

የሆርሙዝን ሰርጥ ማስከፈት የዓለም አጀንዳ በሆነበት ሁኔታ፣ ቀይ ባሕር ቢዘጋ ማስከፈት ከኢትዮጵያ በላይ ለማንም አጀንዳ ሊሆን እንደማይችልና አሁን ባለው ሁኔታም እንደ ምስራቅ አፍሪካ ተጎጂ አለመኖሩንም ጠቁመዋል፡፡

ኢትዮጵያ ከአጭር ጊዜ አንጻር በንግድ ቀጠናዎች ላይ እየሰራች መሆኑን ገልጸው፣ በጂቡቲ መስመር እንዲሁም ሞጆ እና ድሬደዋ ጨምሮ ደረቅ ወደቦች ላይ እየተሰራ እንደሚገኝ አመልክተዋል። እነዚህም ወደቦች ከውጭ የሚገባውን ምርት ፍሰት ለማቀላጠፍና ዋጋ ለመቀነስ እንደሚያግዙ አንስተዋል።

ከረጅም ጊዜ አንጻር ግን ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት ካልሆነች ለዕድገቷ ማነቆ ብቻ ሳይሆን ቀጣናው ሰላም እንደማያገኝና የዓለም ንግድም እንደሚስተጓጎል ጠቅሰዋል፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ያሉ ትላልቅ አቅም ያላቸው ሀገራት ከጉዳዩ ርቀው ከሄዱ፣ ትናንሽ ሀገራት የንግድ ወሽመጦችን መጠበቅ ስለማይችሉ ይህም በዓለም ላይ አደጋ እንደሚያመጣ ገልጸዋል።

ስለሆነም የኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤትነት ጉዳይ ክርክር የማያስፈልገው፣ በሰላም፣ በንግግር እና በድርድር የግድ መፈታት ያለበት ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከባሕር በር ተነጥላ እስከ ወዲያኛው ትኖራለች ብሎ የሚያስብ አካል ካለ የዋህ መሆኑንና የህልውና ጉዳይ ላይ ድርድር በማድረግ ብልጽግናን ማሰብ እንደማይቻል አስገንዝበዋል።

ጉዳዩ ብዙ መሞከርንና አማራጮችን ማየትን የሚጠይቅ ቢሆንም፣ በአጭርና በረጅም ጊዜ ተከፍሎ ሊሰራበት የሚገባ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሳስበዋል። ይህ ካልተከወነ ኢንዱስትሪው በፈለገው ልክ ተወዳዳሪ እንዳይሆን ከማድረጉም ባለፈ ጥራት፣ ጊዜ እና የሎጅስቲክስ ወጪ ላይ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መቅረፍ እንደማይቻል ገልጸዋል።

የባሕር በር ጉዳይ ለእያንዳንዱ ዜጋ፣ ለኢትዮጵያ ብልጽግና፣ ለቀጣናው ሰላም እና ለጋራ እድገት አንገብጋቢ መሆኑን መገንዘብ አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባነሷቸው ሀሳቦች የሚስማሙት ፖለቲካል ሳይንስና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ባለሙያው አቶ አህመድ ሰይድ እንደሚሉትም ለአንድ ሀገር የባሕር በር የፖለቲካ፣ የሥልጣኔ እና አጠቃላይ ብሔራዊ ልማት ማጎልበቻ መሳሪያ ነው፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያም ባሕር በር ያስፈልጋታል ስንል እንዲህ በቀላሉ በመተላለፊያነት ብቻ የሚመዘን ሳይሆን ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ገበናን መሸሸጊያ ወደ ስልጣኔ ማማ መመንደጊያም ጉልበት ነው ባሕር በር ጉዳይ፡፡

በዓለማችን የባሕር በሮች ከሸቀጦች መተላለፊያነት ባሻገር ሀሳቦች የሚፈሱባቸው የደም ሥርም ናቸው የሚሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) በሌላ በኩልም ቀጥተኛ የባሕር መዳረሻ ያላቸው ሀገሮች አስፈላጊ ሀብቶችን ማስገባት እና ምርቶቻቸውን በብቃት ወደ ውጭ መላክ ይችላሉ፡፡ ይህ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ያጠናክራል፡፡ ሀገራት በዓለም አቀፍ ገበያዎች ውስጥ በጥልቀት እንዲዋሃዱ ያስችላቸዋል። በተቃራኒው፣ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ብዙውን ጊዜ ከፍተኛ የትራንስፖርት ወጪዎችን እና የሎጂስቲክስ ፈተናዎች ያጋጥማቸዋል፤ ይህም ተወዳዳሪነትን እና ሁለንተናዊ ልማትን ሊገድብ ይችላል።

የባሕር በር አስፈላጊነት ከኢኮኖሚክስ በላይ ነው የሚሉት ፖለቲካል ሳይንስ ባለሙያው፣ ይሄውም በፖለቲካ ኃይል እና በዓለም አቀፍ ግንኙነቶች ውስጥ ወሳኝ ሚና ይጫወታል። የባሕር መዳረሻ አንድ ሀገር ከድንበሯ ባሻገር ተጽዕኖ እንዲያሳድር ያስችለዋል፡፡

በንግድ ሽርክናዎች፣ በባሕር ኃይል መኖር እና በዓለም አቀፍ የመርከብ መስመሮች ውስጥ በመሳተፍ፣ ቁጥጥር ወይም ስትራቴጂካዊ የውሃ መስመሮችን ማግኘት የአንድን ሀገር የጂኦ ፖሊቲካዊ ጠቀሜታ ከፍ ያደርገዋል፡፡ ይህም በክልላዊ እና በዓለም አቀፍ ጉዳዮች ውስጥ ቁልፍ ሚና እንዲጫወት ያደርገዋል። በታሪክ፣ ኃያላን ሀገሮች ይህንን በሚገባ ተረድተው ፍላጎቶቻቸውን ለማስጠበቅ በባሕር ኃይል ጥንካሬ እና በወደብ መሠረተ ልማት ላይ ከፍተኛ ኢንቨስት እያደረጉ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

የባሕር መዳረሻ የአንድ ሀገር ኢኮኖሚን በበርካታ ዘርፎች በማገናኘት አጠቃላይ ልማትን ያፋጥናል የሚሉት በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሀብት ምሁር ይንገስ አለሙ (ዶ/ር) ዓለም በቅርብ ዓመታት ውስጥ የ‘ሰማያዊ ኢኮኖሚ’ ዓሊያም የውሃን ወይም የባሕር በርን ፋይዳ በእጅጉ እየተረዳው መጥቷል፡፡ ለአብነትም ሆርሙዝ መተላለፊያ መዘጋት ምን ያህል በዓለም ኢኮኖሚ ላይ ጫና እየፈጠረ መምጣቱን እያየነው ያለው እውነት መሆኑን በአስረጅነት ጠቅሰዋል፡፡

“ባሕር እና ሥልጣኔ፤ የዓለም የባሕር ታሪክ” (The Sea and Civilization A Maritime History of the World) በሚል እርዕስ እ.ኤ.አ ሰኔ 2015 ሊንከን ፔይን ባሳተሙት መፅሐፍ ላይ እንደሰፈረው የዓለማችን ስልጣኔ ዞሮ ዞሮ መነሻውና መድረሻው የባሕር በር ነው ይላሉ፡፡

በመለሰ ተሰጋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review