ከየትኛውም ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት የለኝም – ኦብነግ

You are currently viewing ከየትኛውም ታጣቂ ቡድን ጋር ግንኙነት የለኝም – ኦብነግ

AMN – ሰኔ 01/2018 ዓ.ም

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው መባሉን ውድቅ አደረገ።

ኦብነግ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለገባው የሰላም ስምምነት ያለውን ጽኑ ቁርጠኝነትም አረጋግጧል።

ድርጅቱ ባወጣው መግለጫ፤ ከታጠቁ ኃይሎች ጋር ፈጽሞ እንደማይተባበር፣ ስለ ድርጅቱ ወቅታዊ የአመራር ለውጥ እና በትክክለኛ የአሠራር መስመሮች ላይ ብቻ መደገፍ ስለሚያስፈልግበት ሁኔታ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥቷል። ኦብነግ በዚህ ጉዳይ ላይ የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል ቀጥሎ ቀርቧል፡-

ኦብነግ ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው መባሉን ውድቅ አደረገ

የኦጋዴን ብሔራዊ ነጻነት ግንባር (ኦብነግ) ከታጠቁ ቡድኖች ጋር ግንኙነት አለው መባሉን በጽኑ የሚቃወም ሲሆን፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ለተፈረመው የሰላም ስምምነት ያለውን የማይናወጥ ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣል፤ የስምምነቱን ድንጋጌዎች በሙሉ ለማክበር እና ተግባራዊ ለማድረግ ያለውን ዝግጁነትም ያረጋግጣል። በተመሳሳይ ኦብነግ የኢትዮጵያ መንግሥት የገባውን ቃል እንዲያከብር እና የስምምነቱን ሙሉ አፈጻጸም በቅን ልቦና እንዲያረጋግጥ ይጠብቃል።

በጥቅምት 21 ቀን 2018 በአስመራ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ዛሬ በሶማሊ ክልል ለሚታየው ሰላምና መረጋጋት እንደ መሠረት ሆኖ አገልግሏል። ስምምነቱ ከተተገበረበት ጊዜ ጀምሮ ክልሉ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ሰላማዊና የተረጋጉ ክልሎች አንዱ ለመሆን የበቃ ሲሆን፣ ይህም የስምምነቱን አስፈላጊነት እና ሁሉም ወገኖች ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳያል።

ኦብነግ የአስመራው የሰላም ስምምነት ለሶማሊ ክልልና ለሰፊው የአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ጥቅም እንዳስገኘ ያምናል። ከዚህም በላይ ኦብነግ በታሪኩ ሲታገላቸው የነበሩ በርካታ ዓላማዎች እንዲሳኩ አወንታዊ አስተዋጽኦ አድርጓል።

በመሆኑም ኦብነግ በሶማሊ ክልል የተገኘውን ሰላም፣ መረጋጋት እና ልማት ሊያናጋ የሚችል ማንኛውንም ድርጊት ወይም ባህሪ በጥብቅ ይቃወማል። እንዲሁም በሰላም ስምምነቱ አማካኝነት የግል ፍላጎታቸውን ማሳካት ያቃታቸው ጥቂት ግለሰቦች አዲስ ግጭት ለመቀስቀስ በመሞከር የድርጅቱን ስም ያለፈቃድ መጠቀማቸውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ ያደርጋል።

ኦብነግ መሰል ጥረቶች የድርጅቱን መርሆዎች እንደማያንጸባርቁ ወይም የሶማሊ ክልልን እና የሕዝቡን ጥቅም እንደማያገለግሉ ያምናል። ይልቁንም እነዚህ ጥረቶች በክልሉ የተገኘውንና በብዙ ልፋት የመጣውን ሰላምና መረጋጋት ጥርጥር የሌለው አደጋ ላይ የሚጥሉ ሲሆን፣ ከክልሉ ውጪ የሆኑና ከሶማሊ ክልል ሕዝብ ሕጋዊ ምኞት ጋር የሚጋጩ አጀንዳዎችን የሚያራምዱ ናቸው።

በተጨማሪም ኦብነግ አሁን ያለውን የኢትዮጵያ መንግሥት ለመጣል ዓላማ ካላቸው ሌሎች ድርጅቶች ጋር ምንም ዓይነት ጥምረት እንዳልመሠረተ ለሁሉም የሚመለከታቸው አካላት ግልጽ ማድረግ ይሻል።

በሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት በኃይል ለማስወገድ መታገል ወይም ብቸኛ ዓላማቸው የመንግሥትን ሥልጣን በትጥቅ መያዝ ከሆኑ ድርጅቶች ጋር መሳተፍ የኦብነግ ዓላማ ሆኖ አያውቅም። የኦብነግ ተልዕኮ ሁልጊዜም የሶማሊ ክልል ሕዝቦችን መብት፣ ጥቅም እና ምኞት ማስከበር ላይ ያተኮረ ነው። እነዚህን ዓላማዎች በውይይት እና በጋራ ስምምነት መርሆዎች ላይ በመመሥረት፣ በሰላማዊና በዲሞክራሲያዊ መንገድ ለማሳካት ቁርጠኛ ሆኖ ይቀጥላል።

ስለሆነም ኦብነግ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በግጭት ውስጥ ከሚሳተፉ የታጠቁ ቡድኖች ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት፣ ትብብር ወይም ተሳትፎ እንደሌለው በድጋሚ ያረጋግጣል። ኦብነግ ለሰላማዊ ግንኙነቶች ሙሉ በሙሉ ቁርጠኛ ሆኖ የሚቀጥል ሲሆን፣ የሶማሌ ክልልን ሰላም፣ መረጋጋት እና የሕዝብ ጥቅም አደጋ ላይ የሚጥሉ ማናቸውንም ድርጊቶች ውድቅ ያደርጋል።

ኦብነግ አክሎም ከድርጅቱ ምንም ዓይነት ውክልና እና ፈቃድ ሳይኖራቸው በተናጠል በንቀሳቀሱት የቀድሞው የፓርቲው ሊቀመንበር በአቶ አብዲራህማን ማህዲ አማካኝነት የድርጅቱ ስም ያለአግባብ ጥቅም ላይ መዋሉን ያብራራል። አቶ አብዲራህማን ማህዲ በአሁኑ ወቅት በኦብነግ ፓርቲ ውስጥ ምንም ዓይነት የአመራር ቦታ የሌላቸው ሲሆን፣ ፓርቲውን፣ ፖሊሲዎቹን ወይም ዓላማዎቹን አይወክሉም።

እ.አ.አ በሰኔ 2025 በጅጅጋ በተካሄደው የኦብነግ ጉባኤ ላይ አቶ አብዲራህማን ማህዲ ከሊቀመንበርነት ኃላፊነታቸው በይፋ የተነሱ ሲሆን፣ አቶ አብዲካሪም ሼክ ሙሴ የኦብነግ ፓርቲ አዲስ ሊቀመንበር ሆነው በሥርዓቱ ተመርጠዋል። በመሆኑም ከዚያ ቀን በኋላ በአቶ አብዲራህማን ማህዲ የተወሰዱ ማናቸውም እርምጃዎች፣ የተላለፉ ውሳኔዎች ወይም የተሰጡ መግለጫዎች የኦብነግ ፓርቲን ይፋዊ አቋም የማይወክሉ በመሆናቸው እንደ ግል አመለካከታቸውና ተግባራቸው ሊቆጠሩ ይገባል።

የኦብነግ ፓርቲ @ONLFofficial በሚል የሚታወቀው የኤክስ (የቀድሞው ትዊተር) አካውንት የፓርቲው ይፋዊ አካውንት እንዳልሆነ መግለጽ ይወዳል። ይህ አካውንት በአቶ አብዲራህማን ማህዲ የሚተዳደር የግል አካውንት ሲሆን፣ በዚህ አካውንት አማካኝነት የሚታተሙ ይዘቶች የኦብነግ ፓርቲን ይፋዊ ፖሊሲዎች፣ አቋሞች ወይም መግለጫዎች አይወክሉም።

ኦብነግ ሁሉም የሚመለከታቸው ወገኖች፣ ደጋፊዎች፣ የሚዲያ ድርጅቶች እና የሕዝብ አባላት ጥንቃቄ እንዲያደርጉ እና ስለ ፓርቲው አቋም እንዲሁም እንቅስቃሴዎች መረጃ ለማግኘት በይፋ በተፈቀዱ የአሠራር መስመሮች ላይ ብቻ እንዲደገፉ ያሳስባል ማለቱን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review