AMN – ሚያዝያ 20/ 2018 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ መዲናዋ የታሪክ ቅርሶቿን ጠብቃ በማቆየት፣ የነዋሪዎቿን የኑሮ ጫና በመቀነስ እና ዓለም አቀፍ የቱሪዝም ማዕከል በመሆን ረገድ ከፍተኛ ውጤት እያስመዘገበች መሆኗን ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ ከተማዋን የንግድ፣ የዲፕሎማሲ እና የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ የተጀመሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ተጨባጭ ለውጦችን እያመጡ መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ የነዋሪውን የኑሮ ጫና ለመቀነስ በአምስቱ የከተማዋ መግቢያ በሮች ላይ ስድስት ግዙፍ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ መሆኑንም በሪፖርታቸው አንስተዋል።

እነዚህ ማዕከላት ምርቶች ያለምንም ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ከአምራቹ ወደ ሸማቹ እንዲደርሱ በማድረግ ረገድ ትልቅ ሚና እየተጫወቱ ነዉ።
አክለውም መንግስት በትራንስፖርት፣ በጤና፣ በምግብ እና በትምህርት ቁሳቁስ ድጎማ በዓመት 18 ቢሊዮን ብር ገደማ ወጪ እያደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
የዓድዋ ድል መታሰቢያ ግንባታም የኢትዮጵያውያንን አንድነት እና ክብር ከፍ ያደረገ ትልቅ ታሪካዊ ስራ ሆኗል። እንደ ራስ መኮንን ድልድይ፣ የቀድሞ ሲኒማ ቤቶች እና መዘጋጃ ቤትን የመሳሰሉ ነባር ታሪካዊ ቅርሶች መታደሳቸውንም ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል።
የከተማዋን የታሪክ አሻራ በጠበቀ መልኩ የተከናወኑት እነዚህ ተግባራት የአዲስ አበባን የታሪክ ማዕከልነት ዳግም እንዲያንሰራራ አድርገዋል።

በሌላ በኩል አዲስ አበባ የዓለም አቀፍ ስብሰባዎች እና የቱሪዝም ማዕከል የመሆን ጉዞዋን በከፍተኛ ፍጥነት እያሳካች መሆኑን የጠቆሙት ከንቲባዋ፤ ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ200 በላይ ስብሰባዎች በመዲናዋ መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
ይህ የኮንፍረንስ ቱሪዝም ዕድገት ለከተማዋ ተጨማሪ ገቢ ከማስገኘቱም በላይ በሆቴል፣ በንግድ እና በትራንስፖርት ዘርፎች ሰፊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ፈጥሯል።
በወርቅነህ አቢዮ