AMN- ሚያዝያ 24/2018 ዓ.ም
የ75ኛው ዓመት የኮሪያ ዘመቻ መታሰቢያ በዓል በተለያዩ መርሐ ግብሮች በኮሪያ ዘማቾች መታሰቢያ ፓርክ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡
በመርሐ ግብሩ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር፣ ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ኃላፊዎች፣ በወቅቱ ጦራቸውን ወደ ደቡብ ኮሪያ የላኩ መንግስታት አምባሳደሮች ወታደራዊ አታሼዎች፣ የዓለም አቀፍ ድርጅት ኃላፊዎች፣ ከአዲስ አበባና ከክልሎች የመጡ አርበኞች ተሳትፈዋል።
በዘማች ወታደሮች መታሰቢያ ሃውልት የአበባ ጉንጉን የማኖር ሥነ ስርዓትም ተከናውኗል።
በኮሪያ ምድር ጦርነት በተቀሰቀሰበት ወቅት የተባበሩት መንግስታት ደርጅት በቻርተሩ መሰረት ለኢትዮጵያ ጥሪ ሲያደርግላት ወዲያውኑ ተቀብላ ወታደሮቿን ወደ ስፍራው አዝምታለች።
በወቅቱም ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም መጠበቅ ያላትን ፅኑ ፍላጎትና ለገባችው ቃል ኪዳን ታማኝነቷን ያሳያችበትና ያሰመሰከረችበት ወቅት እንደነበረ፣ የኢትዮጵያ የኮሪያ ዘማቾች ማህበር ፕሬዚዳንት ኮሎኔል እስጢፍኖስ ገብረ መስቀል ባደረጉት ንግግር አስታውሰዋል።
የኮሪያ ዘማቾች ያስመዘገቡት አኩሪ ታሪክ ሊረሳ የማይችል መሆኑን ጠቅሰው፣ ይህም በታሪክ ሲታወስና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፍ አኩሪ ታሪክ መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ የኮሪያ አምባሳደር ጁንግ ካንግ በበኩላቸው፣ ከ75 ዓመት በፊት የኢትዮጵያ ወታደሮች በኮሪያ ልሳነ ምድር ለኮሪያ ሰላምና ነፃነት ላበረከቱት አስተዋጾኦ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።
የኮሪያ ዘማቾች የምን ጊዜም የኮሪያና የህዝቦቿ ጀግና መሆናቸውን ጠቅሰው፣ የሁለቱ ሀገራት ትብብርና ትስስር የበለጠ ለማጠናከር እንደሚሠራም ተናግረዋል።
በቤተልሔም አየነው