የአርሰናል የፍጻሜ ጉዞ ታሪክ

You are currently viewing የአርሰናል የፍጻሜ ጉዞ ታሪክ

AMN- ሚያዚያ 27/2018 ዓ.ም

አርሰናል በታሪኩ ለታላቁ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ያለፈው አንድ ጊዜ ብቻ ነው።

ይህም እ.ኤ.አ. በ2006 በፈረንሳይ ፓሪስ ከባርሴሎና ጋር የተጫወተበት ሲሆን፣ በወቅቱ 2 ለ 1 በሆነ ውጤት መሸነፉ ይታወሳል።

ዘንድሮ አርሰናል ይህንን ታሪክ ለመድገም እና ለሁለተኛ ጊዜ ለፍጻሜ ለመድረስ እየተፋለመ ይገኛል።

በአውሮፓ ካፕ ዊነርስ ካፕ ሶስት ጊዜ ለፍጻሜ ደርሶ አንዱን (በ1994) አሸንፏል፡፡ በዩሮፓ ሊግ ሁለት ጊዜ (በ2000 እና 2019) ለፍጻሜ ደርሶ በሁለቱም ተሸንፏል።

በሚካኤል አርቴታ የሚመራው አርሰናል በ2025/26 የውድድር ዘመን እጅግ ጠንካራ ተፎካካሪ ሆኖ ቀጥሏል። በተለይም በፕሪምየር ሊጉ እና በሻምፒዮንስ ሊጉ የሚያሳየው ብቃት ለደጋፊዎቹ ትልቅ ተስፋን ሰጥቷል።

አርሰናል ባለፉት ጥቂት አመታት ከአውሮፓ መድረክ ርቆ ከቆየ በኋላ፣ አሁን ላይ ካሉት የአውሮፓ ምርጥ ስድስት ክለቦች ተርታ ተመድቧል። ክለቡ በተለይ በሜዳው (ኤምሬትስ ስታዲየም) ያለው አስፈሪ ብቃት እና የተከላካይ መስመሩ ጥንካሬ ለሁለተኛው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍጻሜ ጉዞው እንደ ዋና መሳርያ እየተጠቀመበት ይገኛል።

በዘንድሮው የውድድር ዘመን አርሰናል በሊጉም ሆነ በአውሮፓ ጥቂት ግቦችን የተቆጠሩበት ቡድን ነው። የዊልያም ሳሊባ እና ገብርኤል ማጋልሄስ ጥምረት ለቡድኑ መረጋጋትን ሰጥቷል። በተጨማሪም ፣ ቡድኑ ካለፉት ዓመታት በተሻለ ሁኔታ በስነ-ልቦና መጎልበቱ ለወሳኝ ጨዋታዎች ዝግጁ እንዲሆን አድርጎታል።

አርሰናል የፕሪምየር ሊጉን ዋንጫ ለ22 አመታት፣ የሻምፒዮንስ ሊጉን ደግሞ በታሪኩ አንዴም አላነሳም። በመሆኑም ዘንድሮ ይህንን ድርቅ ለመስበር በከፍተኛ ተነሳሽነት ላይ ይገኛል። ቡድኑ ወጥ የሆነ ብቃት እያሳየ በመሆኑ፣ እስከ ፍጻሜው ለመጓዝ ያለው እድል ሰፊ እንደሆነ የስፖርት ተንታኞች ይስማማሉ።

አርሰናል እና አትሌቲኮ ማድሪድ በአውሮፓ እግር ኳስ መድረክ በተለይም በሻምፒዮንስ ሊግ ታሪካቸው ውስጥ የሚጋሯቸው በርካታ አስገራሚ ተመሳሳይነቶች አሏቸው።

ሁለቱም ክለቦች ለዋንጫው በጣም ተቃርበው በሽንፈት ተመልሰዋል፡፡ አርሰናል በ2006 ፍጻሜ ላይ እስከ 76ኛው ደቂቃ ድረስ 1 ለ 0 እየመራ ቢቆይም፣ በስተመጨረሻ በባርሴሎና 2 ለ 1 ተሸንፏል።

አትሌቲኮ ማድሪድ በተለይ በ2014 እና 2016 ለፍጻሜ ደርሶ፣ በሁለቱም አጋጣሚዎች በከተማ ተቀናቃኙ ሪያል ማድሪድ በጭማሪ ሰዓት እና በመለያ ምት ተሸንፎ ዋንጫ አጥቷል።

በአውሮፓ እግር ኳስ ተንታኞች ዘንድ “ሻምፒዮንስ ሊግን ለማሸነፍ ከሚገባቸው ግን ካላሸነፉ” ምርጥ ክለቦች ዝርዝር ውስጥ ሁለቱም ክለቦች ሁልጊዜም በግንባር ቀደምትነት ይጠቀሳሉ። ሁለቱም ክለቦች በየዘመናቸው የአውሮፓን ምርጥ ክለቦች የሚያስቸግር ቡድን ቢኖራቸውም፣ ዋንጫውን ለመሳም ግን አልታደሉም።

ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚደረገው የግማሽ ፍጻሜ የመልስ ጨዋታ ለፍጻሜ ለማለፍ በሚደረገው ፍልሚያ አርሰናል የተሸለ ግምት አግኝቷል፡፡

በቶለሳ መብራቴ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review