AMN ግንቦት 5/2018
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ትብብርና ለባለብዙ ወገን ግንኙነት ያላትን ቁርጠኝነትና ተምሳሌትነት አደነቁ።
ኢትዮጵያ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስምንት አስርት ዓመታት ጉዞን ምክንያት በማድረግ፣ “በሰላም አብሮ ለመኖር” በሚል መሪ ቃል ልዩ የመታሰቢያ ቴምብር ስብስብ አውጥታለች።
የተመድ ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በዚሁ ወቅት ባደረጉት ንግግር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሁነቱን በማዘጋጀታቸውና የኢትዮጵያ ህዝብ ላደረገላቸው ደማቅ አቀባበል ምስጋና አቅርበዋል።

ልዩ የመታሰቢያ ቴምብሩ ለተመድ 80ኛ ዓመት ምስረታ ከመዘከር ባለፈ ተመድ እና ኢትዮጵያ ያላቸውን የረጅም ጊዜ ግንኙነት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ኢትዮጵያ እ.አ.አ በ1945 ተመድ በሳን ፍራንሲስኮ ሲመሰረት ቻርተሩን ከፈረሙ 51 ሀገራት መካከል አንዷ እንደሆነች አውስተዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የባለብዙ ወገን እና ዓለም አቀፍ ትብብር ተምሳሌት ሆና መቀጠሏን አመልክተዋል።
ኢትዮጵያ ጥንታዊ ስልጣኔን የምትወክል ሀገር ናት ያሉት ዋና ፀሐፊው በዓለም ላይ ፈጣን የኢኮኖሚ እድገት እያስመዘገቡ ካሉ ሀገራት መካከል አንዷ መሆኗንም አንስተዋል።