ኢትዮጵያ ከሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ድምፅና የዓለም ሰላም ተሟጋች

You are currently viewing ኢትዮጵያ ከሊግ ኦፍ ኔሽን እስከ የተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካ ድምፅና የዓለም ሰላም ተሟጋች

AMN- ግንቦት 6/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ታሪክ ውስጥ ያላት ሚና የቆየና በጽኑ መርህ ላይ የተመሠረተ መሆኑ ተገለጸ።

ከሊግ ኦፍ ኔሽን ምስረታ ጀምሮ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን (UN) ከመሰረቱት ጥቂት አገራት አንዷ በመሆን፣ የሉዓላዊነት እና የጋራ ደህንነት ተሟጋች ሆና ዘልቃለች።

በተለይም የአፍሪካ ድምፅ በዓለም መድረክ እንዲሰማ እና አህጉሪቱ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫ እንዲኖራት የምታደርገው ጥረት የዲፕሎማሲያዊ እንቅስቃሴዋ ማዕከል ሆኖ ቀጥሏል።

ኢትዮጵያ ለዓለም ሰላም ያላትን ቁርጠኝነት በተግባር ካሳየችባቸው መስኮች ቀዳሚው የሰላም ማስከበር ስምሪት ነው።

እ.ኤ.አ. በ1950ዎቹ በኮሪያ ዘመቻ የጀመረው ይህ ተሳትፎ፤ በኮንጎ፣ በሩዋንዳ፣ በብሩንዲ፣ በላይቤሪያ፣ በሱዳን (ዳርፉር እና አብዬ) እንዲሁም በሶማሊያ በስኬት ቀጥሏል።

በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ ለተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሰላም አስከባሪ ኃይል ከሚያዋጡ አገራት ተርታ የምትመደብ ሲሆን፤ ይህም አገሪቱ ለቀጣናዊ እና ለዓለም አቀፋዊ መረጋጋት ያላትን የማይናወጥ አቋም ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
በተባበሩት መንግሥታት መድረክ የኢትዮጵያ መሪዎች ያስተላለፏቸው መልእክቶች በትውልድ የሚታወሱ ናቸው።

ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ እ.ኤ.አ በ1936 በሊግ ኦፍ ኔሽን ያደረጉት ንግግር፣ የጋራ ደህንነት ካልተከበረ ዓለም ወደ ቀውስ እንደምትገባ ያስጠነቀቁበት ታሪካዊ ክስተት ነበር።

በቅርቡ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተለያዩ ዓለም አቀፍ መድረኮች አፍሪካ በጸጥታው ምክር ቤት ቋሚ መቀመጫና ተመጣጣኝ ውክልና ሊኖራት እንደሚገባ በመግለጽ ታሪካዊ ጥሪ አቅርበዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከ1.4 ቢሊዮን በላይ ሕዝብ ያቀፈችው አፍሪካ በምክር ቤቱ ውስጥ ቋሚ ድምፅ አልባ መሆኗ ፍትሃዊነት የጎደለውና ወቅታዊውን የዓለም ፖለቲካዊ ነባራዊ ሁኔታ የማይወክል መሆኑን በማጉላት፣ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ለዚህ ጥያቄ ተግባራዊ ምላሽ እንዲሰጥ አንስተዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ፣ አገሪቱ ለድርጅቱ ምስረታ እና ለሰላም ማስከበር ሥራ ያበረከተችውን አስተዋጽኦ በከፍተኛ ደረጃ አድንቀዋል።

ዋና ጸሐፊው ኢትዮጵያን “የአፍሪካ የነጻነት ተምሳሌት እና የተባበሩት መንግሥታት ታማኝ አጋር” በማለት ገልጸዋታል።

ኢትዮጵያ “ለአፍሪካ ችግሮች አፍሪካዊ መፍትሄ” የሚለውን መርህ በማንገብ፣ የአባልነት መብት እንድታገኝ የምታደርገው ተከታታይ ትግል፣ የአፍሪካ ሕብረትን የጋራ አቋም መሠረት ያደረገ መሆኑም ተመላክቷል።

ይህ ሁኔታ ኢትዮጵያ ባለፉት 80 ዓመታት በዓለም መድረክ የነበራትን የዲፕሎማሲ የበላይነት እና ወደፊትም የሚኖራትን ፋይዳ ዳግም ያረጋገጠ ሆኖ ተመዝግቧል።

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review