አዲስ አበባ- ለህጻናትና ወጣቶች ዕድገት ተመራጯ መዲና

You are currently viewing አዲስ አበባ- ለህጻናትና ወጣቶች ዕድገት ተመራጯ መዲና

AMN- ግንቦት 18/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች የሚኖሩባት ዋነኛ የሀገሪቱ ብሎም የአፍሪካ መዲና ናት፡፡

አዲስ አበባ ለንግድ፤ ለኢንቨስትመንት እና ለኑሮ ተመራጭ መዲና ብትሆንም፣ ህብረተሰቡ አካታች የልማት ተጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ ጋር ተያይዞ ግን በርካታ ውስንነቶች ነበሩ፡፡

በተለይ በመዲናዋ ሲተገበሩ የነበሩ የልማት ሥራዎች የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናትና ወጣቶችን የዘነጉ በመሆናቸው ታዳጊዎቹ ከአልባሌ ሥፍራዎች ርቀው የነገውን ህይወታቸውን ዛሬ ላይ የሚቀርጹባቸውን ማዕከላት ለማግኘት አልታደሉም፡፡

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን የከተማ አስተዳደሩ ለነገ ሀገር ተረካቢዎች በሰጠው ልዩ ትኩረት አዲስ አበባ ከንግድና ኢንቨስትመንት ጎን ለጎን የህጻናትና ወጣቶች መዲና ለመሆን በቅታለች፡፡

በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም አቅጣጫዎች ህጻናት ቦርቀው የሚጫወቱባቸውንና ወጣቶች ስፓርታዊ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉባቸውን ማዕከላት መመልከትም የተለመደ ሆኗል፡፡

ወላጆችና አሳዳጊዎችን ጨምሮ አዛውንቶችና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ሩቅ ሳይሄዱ በአቅራቢያቸው ልጆቻቸውን እያጫወቱ ራሳቸውም የሚዝናኑባቸውን ቦታዎች አግኝተዋል፡፡

እነዚህ የመጫወቻና የስፓርት ማዕከላት፣ ህጻናትና ወጣቶች ከአልባሌ ቦታዎች ርቀው፤ ስቀውና ቦርቀው የሚጫወቱባቸው ብቻ ሳይሆኑ፣ ትምህርትና መልካም ሥነ ምግባርን፤ ማህበራዊ መስተጋብርን እና አብሮ መኖርን የሚለማመዱባቸው ሥፍራዎችም ሆነዋል፡፡

የከተማ አስተዳደሩ ባለፉት 9 ወራት ብቻ ከ5 ሺህ በላይ የልጆች መጫወቻዎችን እና ከ1 ሺህ በላይ የህጻናት ማቆያዎችን ገንብቶ ለአገልግሎት ማብቃቱም መስተዳደሩ ለህጻናት እድገትና ክብካቤ የሰጠውን ልዩ ትኩረት የሚያረጋግጥ ነው፡፡

ወጣቶች በአእምሮና በአካል ዳብረው የሚያድጉባቸው በርካታ የስፖርት ማዘውተሪያዎች በየሰፈሩ መገንባታቸው እና ትላልቅ ስታዲየሞችም በመገንባት ላይ መሆናቸውም የከተማ አስተዳደሩ አካታች መሰረተ ልማትን እውን ለማድረግ ያለዉን ቁርጠኝነት የሚያሳይ ነዉ፡፡

የመዲናዋ ባለሃብቶችም ሀገር የምትገነባው በህጻናትና ታዳጊዎች መሆኑን በመገንዘብ፣ የበኩላቸውን ሚና በመወጣት ላይ መሆናቸውም የትውልድ ግንባታ ወሳኝ ሀገራዊ ራዕይ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እነዚህ መሰረተ ልማቶች የህጻናትና ታዳጊዎች መጫወጫዎቻና መዝናኛዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ የነገዋን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመመልከት የልጅነት ህልማቸውን የሚስሉባቸው ጭምር ናቸው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በቦሌ ክፍለ ከተማ የተገነቡ የስፖርት ማዘውተሪያዎችን፣ የህጻናት መጫዎቻዎችን፤ የህጻናት ማቆያዎችን፤ አንፊ ትያትሮችንና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመረቁበት ወቅት ባስተላለፉት መልእክት፣ አዲስ አበባን የብልጽግና ተምሳሌት እናደርጋታለን ብለን ስንነሳ በአካልና በአዕምሮ የዳበረ ትውልድ መገንባትን ቅድሚያ በመስጠት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ዓላማ በመነሳትም በከተማዋ በርካታ ዘመናዊ የስፖርት ማዕከላትንና የመጫወቻ ሜዳዎችን በመገንባት ለሕዝብ ጥቅም እንዲውሉ ማድረግ መቻሉንም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

የስፖርት መሠረተ ልማቶች ምቹ የመዝናኛ ስፍራን ከመፍጠር ባሻገር በአካልና በሥነ-ልቦና የታነጸ ዜጋ መቅረጽ ያስችላል ብለዋል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review