የቦረና ሕዝብ ከተረጅነት ነፃ መውጣቱ በተግባር የታየ ትልቅ ለውጥ ነው-ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN ግንቦት 19 /2018

የቦረና ሕዝብ ያሳየው የታታሪነትና የሥራ ወዳድነት መንፈስ የተፈጥሮ ጸጋን ተጠቅሞ ከረሃብ መውጣት እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን ያመለከቱት በምስራቅ ቦረና ዞን ሊበን ወረዳ በሜካናይዜሽን የታገዘውንና በክላስተር እየለማ የሚገኘውን ሰፊ የስንዴ ማሳ በጎበኙበት ወቅት ነው።

የአካባቢው ማህበረሰብ ከጥቂት ዓመታት በፊት ይደርስበት ከነበረው ተደጋጋሚ የድርቅ አደጋና የውኃ እጥረት ፈተና ተላቆ፣ በአሁኑ ወቅት በአረንጓዴ ልማት አዲስ ምዕራፍ እየጻፈ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ቀደም ሲል እስከ 90 በመቶ የሚደርሰው የዞኑ ነዋሪ በሴፍቲኔት ድጋፍ ይተዳደር እንደነበርና ማህበራዊ ሁነቶች እንኳ ሳይቀሩ በእርዳታ እህል ይከናወኑ እንደነበር ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ዛሬ ላይ ግን ያ የድህነት ታሪክ ተቀይሮ የተረጅነት ምጣኔው ወደ ዜሮ መውረዱን ይፋ አድርገዋል።

ይህ በአጭር ጊዜ ውስጥ የተመዘገበውና ማህበረሰቡን ከእርዳታ ጥገኝነት ሙሉ በሙሉ ያላቀቀው ስኬት በቃላት ሊገለጽ የማይችል ተዓምር መሆኑን ገልጸዋል።

በዘንድሮው አውድማ በሊበን ወረዳ ብቻ 250 ሺህ ሄክታር መሬት በስንዴ ሰብል መሸፈኑን ጠቁመው፤ የተሻሻሉ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም ምርታማነቱን ይበልጥ ማሳደግ እንደሚቻልና ይህም ከአገር ውስጥ ፍጆታ ባለፈ ምርትን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ዕድል እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

ቀደም ሲል የረድኤት እህል ይከፋፈልበት የነበረው ስፍራ ዛሬ ወደ ሰፊ የምርት ማዕከልነት ተለውጦ ማየት ታላቅ ደስታን የሚፈጥር መሆኑን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህ አይነቱ አመርቂ የልማት ተሞክሮ በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎችም ሊሰፋ እንደሚገባ አሳስበዋል።

በርትቶ በመስራት ከልመናና ከረሃብ መውጣት እንደሚቻል የቦረና ሕዝብ በተግባር ማሳየቱንም አክለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማጠቃለያቸው፤ የቦረና ሕዝብ ያሳየው ታታሪነት እና የስራ ወዳድነት መንፈስ የተፈጥሮ ጸጋንና እውቀትን አቀናጅቶ በመጠቀም ረሃብንና ጥገኝነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ማስወገድ እንደሚቻል ትልቅ ማረጋገጫ የሰጠ ነው ብለዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review