የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ነፃ፣ አካታችና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስችሉ ስራዎች ተሰርተዋል- ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን

AMN- ግንቦት 20/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት 93 በመቶ የሚሆኑ የሀገሪቱን ወረዳዎች ተደራሽ በማድረግ ከ2 ሺህ በላይ አጀንዳዎችን ማሰባሰብ መቻሉን አስታውቋል፡፡

የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደቱ ነፃ፣ አካታችና ዲሞክራሲያዊ እንዲሆን የሚያስችሉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን የገለጸው ኮሚሸኑ፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት ያከናወናቸውን አበይት ተግባራት፣ የገጠሙትን ተግዳሮቶችና በቀጣይ ስራዎች ላይ ዛሬ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ኮሚሽኑ ካሰባሰባቸው ጉዳዮች መካከል ለሀገራዊ ምክክሩ ወሳኝ ናቸው ያላቸውን ጉዳዮች በረቂቅ አጀንዳነት በማደራጀት አመካካሪዎችን ዝግጁ የማድረግ ስራ እያከናወነ እንደሚገኝም ገልጿል።

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት የኮሚሽኑ ዋና ኮሚሽነር ፕሮፌሰር መስፍን አርአያ እንደገለጹት፣ ኮሚሽኑ ከተቋቋመበት ጊዜ አንስቶ በመንግስትና በህዝብ መካከል ያለውን ግንኙነት ለማሻሻል፣ መተማመንን ለመፍጠር እንዲሁም ጠንካራና ቅቡልነት ያለው ህገ-መንግስታዊና ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችሉ ተግባራትን ሲያከናውን ቆይቷል።

ለዚህም ስኬት በዲጂታላይዜሽን የተሰናዳ አስተማማኝ የመረጃ ቋት መፈጠሩ ስራውን በዘመናዊ መንገድ ለመምራት ትልቅ እገዛ ማድረጉን ጠቁመዋል።

ይህ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ፍፁም አሳታፊ በሆነ መልኩ የተከናወነ ሲሆን፣ ከፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከመንግስት፣ ከሲቪል ማህበራት፣ ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከሃይማኖት ተቋማት፣ ከህዝብ ተወካዮች፣ ከዲያስፖራና ከዓለም አቀፍ ማህበረሰብ ጋር ገፅ ለገፅ ከመገናኘት ባለፈ፤ ከትላልቅ መድረኮች፣ ለኮሚሽኑ ከቀረቡ ሰነዶችና ቀደም ሲል ከተጠኑ ጥናቶች ጭምር አጀንዳዎች መሰባሰባቸው ተመላክቷል፡፡

ሁሉንም አካባቢዎች የምክክሩ አካል ለማድረግ በተደረገው ጥረት በተለይ በትግራይ ክልል ያለውን ነባራዊ ሁነት በመገንዘብ ከጊዜያዊ አስተዳደሩ ጋር ከ22 ጊዜ በላይ ውይይት ቢደረግም፣ ሂደቱ በክልሉ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ባለመሳካቱ የክልሉ ተወካዮች በተገኙበት በአዲስ አበባ ከተማ የአጀንዳ ማሰባሰብ ስራው ተከናውኗል።

ስለ ፖለቲካ ፓርቲዎች ተሳትፎ ያብራሩት ፕሮፌሰሩ፣ እጅግ በርካታ ፓርቲዎች በሂደቱ ላይ ንቁ ተሳትፎ እያደረጉ መሆኑንና አሁንም ድረስ ሂደቱን በተጠባባቂነት የሚመለከቱ ወጣ ገባ የሚሉ እንዳሉ ገልጸው፤ የታጠቁ ሃይሎችንም በምክክሩ ውስጥ ለማካተት በርካታ ጥረቶች መደረጋቸውንና ይህም አሁንም ሙሉ በሙሉ የተሟላ ባይሆንም ተጨማሪ ጥረቶች በቀጣይም ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ አረጋግጠዋል።

በአሁኑ ወቅት ኮሚሽኑ ረቂቅ አጀንዳዎችን አደራጅቶ ማጠናቀቁን ተከትሎ፣ ለሀገራዊ ምክክር ጉባኤው ስኬት መነሻ የሚሆንና 4 ሺህ ታዳሚዎች የሚሳተፉበት ታላቅ የምክክር ጉባኤ በአዲስ አበባ ከተማ ለአንድ ሳምንት ያህል እንደሚካሄድ ተጠቁሟል፡፡

በራሄል አበበ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review