AMN- ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

ሀገር መጻኢ ዕድሏን የምትወስንበት እና ዜጎች ይበጀኛል የሚሉትን መሪ የሚመርጡበት 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ሊካሄድ ጥቂት ቀናት ብቻ ቀርተውታል።
በዚህ የሀገር ሁለንተናዊ ዕጣ ፈንታ በሚወሰንበት ታሪካዊ ምርጫ ላይ ከ50 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵያውያን ድምፅ ለመስጠት ተመዝግበዋል።
ምርጫው በስኬት ይጠናቀቅ ዘንድ የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች ከምዝገባው ሂደት ጀምሮ ለህዝቡ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ ሲያበረክቱ ቆይተዋል።
የፊንፊኔ አባገዳ ጽሕፈት ቤት እና ግቢ ኃላፊ አባገዳ ፍቃዱ ወንድሙ እንደገለጹት፣ ማንኛውም የምርጫ ካርድ የወሰደ ዜጋ በምርጫው ዕለት መሳተፍ ይኖርበታል።

ማንም ሰው ምርጫ ሳይመርጥ ማለፍ የለበትም ያሉት አባገዳ ፍቃዱ፣ የምርጫ ካርድ መውሰድ እና ካርድ ከወሰዱ በኋላ ይመቸናል፣ ይመጥነናል፣ ያገለግለናል፣ የሚሉትን ፓርቲ ወይም ግለሰብ መምረጥ በጣም አስፈላጊ መሆኑን አንስተዋል።
መምረጥ ግዴታችን ብቻ ሳይሆን ነገአችንን፣ ሀገራችንን፣ ራሳችንን እና እድገታችንን በማሰብ የምናደርገው ውሳኔ ነው ብለዋል።
የሃይማኖት ተቋማት ለህዝቡ ግንዛቤ ከመስጠት ባሻገር፣ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድን በገለልተኝነትና በጥንካሬ የማደራጀት የህግ ድርሻቸውን ሲወጡ መቆየታቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ቀሲስ ታጋይ ታደሰ በበኩላቸው፣ ጉባኤው በአዋጅ በተሰጠው ስልጣን መሰረት የምርጫ ቦርድ ዕጩዎችን በመመልመል ረገድ ትልቅ ኃላፊነት እንደተወጣ አብራርተዋል።
በአሁኑ ወቅት ምርጫ ቦርድን በሰብሳቢነትና በአባልነት እያስተባበሩ ያሉ የቦርዱን አመራሮች፤ ጉባኤው በታማኝነት፣ በስኬት እንዲሁም ሁሉን አሳታፊ በሆነ መልኩ አስመርጧል ሲሉ አስረድተዋል።
የአዲስ አበባ ከተማ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ፕሬዚዳንት ሼኽ ሱልጣን ሐጅ አማን ኤባ፣ አንድ ዜጋ በምርጫ መሳተፉ ሀገራዊ ዜግነቱን የሚያስመሰክርበት ዋነኛ መንገድ መሆኑን ጠቁመዋል።

ብዙ ሰዎች ‘ምርጫ’ ሲባል ቸል የሚሉበት ሁኔታ ይታያል። ነገር ግን ለህዝባዊ መብታችን ትልቁ መገለጫ በምርጫ መሳተፍ፣ ተመዝግቦ ይሠራልኛል የሚሉትን መሪ በነጻነት መምረጥ ነው ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
ከቅድመ ምርጫ ጀምሮ የተሰሩ ሥራዎች ሙሉ ስኬት የሚያገኙት ህዝቡ በወሰደው ካርድ የሀገሪቱን ዕጣ ፈንታ በድምፁ ሲወስን በመሆኑ፣ ሁሉም እምነት ተከታዮች የነገውን መሪ ለመወሰን ድምፃቸውን እንዲሰጡ የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች ጥሪያቸውን አቅርበዋል።
የሀገሪቱ የፖለቲካ ጉዞ ላይ ትልቅ ምዕራፍ ይከፍታል የተባለው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ በቀጣዩ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም በመላ ሀገሪቱ በይፋ ይካሄዳል።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ