AMN- ግንቦት 28/2018 ዓ.ም
በ7ኛው አገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ዕለት የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ከማለዳ ጀምሮ በምርጫ ጣቢያዎች በመገኘት ድምፃቸውን ሰጥተዋል። በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች የታየው ረጅም ሰልፍ የህዝቡን የነቃ ተሳትፎ አሳይቷል።
ከሌሊቱ 11፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ምሽት ድረስ የቀጠለው የምርጫ ሂደት በትዕግስት፣ በሥነ ምግባር እና በሃገራዊ ሃላፊነት ስሜት መከናወኑ ብዙዎችን አስደምሟል። መራጮች ለሰዓታት በሰልፍ ማሳለፋቸው፣ ለዴሞክራሲያዊ መብታቸው ያላቸውን ጽኑ ቁርጠኝነት ያሳየ ሆኗል።

አቶ ዳኛቸው ሽፈራዉ የተባሉ መራጭ አንድ ድምፅ ለሀገር የወደፊት ዕጣ ፈንታ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው በጽኑ በማመን ድምጽ መስጠታቸዉን ተናግረዋል፡፡
ለመጀመሪያ ጊዜ ድምፅ የሰጠችው ሀና ደንበል በበኩሏ፣ የምርጫ ካርዷን ከወሰደችበት ጊዜ ጀምሮ በጉጉት ስትጠብቅ እንደነበረች ተናግራለች።
“ያ በእጄ ያለው ካርድ ተራ ወረቀት ሳይሆን የነገዋን ሀገር የምገነባበት ድምፄ ነው” ያለችው ሀና፣ ለለውጥ ያላት ተስፋ ለሰዓታት በሰልፍ እንድትቆም እንዳስገደዳት ገልጻለች።
በሰባቱም ሃገራዊ ምርጫዎች ተሳትፎ ያደረጉት ሄኖክ ጥላሁን፣ የምርጫ ካርድ መውሰድና ድምፅ መስጠት የእያንዳንዱ ዜጋ ዋነኛ ኃላፊነት መሆኑን ገልጸዋል።
“እውነተኛና ዘላቂ ለውጥ የሚመጣው በኃይል ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ በምናስቀምጠው የምርጫ ካርድ ነው” ሲሉም የምርጫውን ዋና መልዕክት አስቀምጠዋል።

ለሰባት ጊዜ ያህል ድምፃቸውን የሰጡት አቶ ወንድሙ ሻቃ በበኩላቸው፣ በምርጫ ጣቢያዎች የታየው የሰላም ባህል፣ የመከባበር መንፈስና የትዕግስት ጉዞ ሀገሪቱ ወደ የተሻለ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እየተሸጋገረች መሆኗን ያሳያል ብለዋል።
በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው ረጅም ሰልፍ የመጠባበቅ ትዕይንት ብቻ ሳይሆን፣ ህዝቡ በሰላም፣ በሕግና በዴሞክራሲ መንገድ ሀገሩን ለመገንባት ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየ ታሪካዊ መልዕክት ሆኖ ተመዝግቧል።
ዝርዝር መረጃዉን ነገ በአዲስ ልሳን ጋዜጣ ይጠብቁ!
በቶለሳ መብራቴ