AMN – ሰኔ 06/2018 ዓ.ም

ለበርካታ አስርት ዓመታት በታሪካዊቷ ፒያሳ በተለይም በሰራተኛ ሰፈር፣ በዶሮ ማነቂያና በእሪ በከንቱ አካባቢዎች ይኖሩ በነበሩበት ወቅት የነበረውን የተጎሳቆለ አኗኗር ሙሉ በሙሉ የቀየረው የኮሪደር ልማት ሥራ፣ የከተማዋን ገጽታ ከመለወጥ ባለፈ የሰዎችን ሕሊናና አመለካከት ጭምር እየፈወሰና ታላቅ መነቃቃትን እየፈጠረ እንደሚገኝ የቀድሞ የፒያሳ ነዋሪዎች ገለጹ።

የቀድሞ ነዋሪዎቹ ለልማቱ ያላቸውን ከፍተኛ አድናቆት እና ኩራትም ለኤ ኤም ኤን አጋርተዋል።
ከ1967 ዓ.ም ጀምሮ ለ48 ዓመታት በፒያሳ ህንድ ትምህርት ቤት አጠገብ ይኖሩ የነበሩት አቶ ኃይለማሪያም ገቢሳ በሰጡት ምስክርነት፣ በአንድ መኖሪያ ቤት ውስጥ በአማካይ ከ10 እስከ 15 የሚደርሱ ሰዎች ይኖሩ ስለነበር፣ ማለዳ ለሥራ በሚነሱበት ወቅት ለሽንት ቤት ረጅም ሰልፍ ለመያዝ ይገደዱ እንደነበርና ታማሚዎች እንኳ መጠጊያ የሚያጡበት ያ ሁኔታ እጅግ የሚሰቀጥጥ እንደነበር በምሬት አውስተዋል።

ሌላኛዋ የአካባቢው የቀድሞ ነዋሪ የነበሩት ወይዘሮ ሮማን ጌታቸው በሰጡት አስተያየት፣ ሰፈሩ በማህበራዊ ኑሮውና በፍቅር የታወቀ የአራዳ መንደር ቢሆንም፣ የዕለት ተዕለት አኗኗራቸው ግን በጭቃና በካርቶን በተሰሩ ጠባብ ቤቶች ውስጥ የተወሰነና እጅግ አስቸጋሪ እንደነበር አስታውሰው፣ አሁን ግን አዲስ አበባ እውነተኛ ስሟን መያዟን አስረድተዋል።

የቀድሞ ነዋሪዎቹ አክለውም፣ ስፍራው ቀድሞ «የወርቅ ሰፈር» እየተባለ ይጠራ እንደነበር ጠቅሰው፤ ነገር ግን ከውስጥና ከጓሮው ሲታይ መሠረታዊ የንጽህና አገልግሎትና የሽንት ቤት መሠረተ-ልማት ያልነበረው፣ የቆሻሻ ክምችት የነበረበት ቦታ እንደነበር ገልጸዋል።
የሀይማኖት መምህሩ ሊቀሊቃውንት አባ ተክለሀይማኖት ወልዱ በበኩላቸው በኮሪደር ልማቱ አማካኝነት አካባቢው ሲነካካና የነበረው አሮጌ ገጽታ ሲገፈፍ፣ ለሰው ልጅ የማይመጥኑና ፍጹም ሊኖርባቸው የማይገቡ በርካታ ስውር ችግሮች በግልጽ ሊታዩና ሊታወቁ እንደቻሉ ተመልካቾችና ነዋሪዎቹ በተጨባጭ መታዘባቸውን አስረድተዋል።

ይህ ታላቅ የልማት ሥራ የነበረውን አስከፊ ገጽታ ሙሉ በሙሉ በመግፈፍ፣ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ላይ ሕፃናት በነፃነት የሚቦርቁበትና የሚያድጉበት፣ ወጣቶች ስፖርት የሚሰሩበት፣ እንዲሁም አረጋውያን ወጥተው ንጹህ አየር እያገኙ ሰውነታቸውን የሚያንቀሳቅሱበት ምቹና ውብ መናፈሻዎችን መፍጠር መቻሉን ነዋሪዎቹ በደስታ አረጋግጠዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ልማቱ ማህበራዊ ፍትህን ያረጋገጠ በመሆኑ፣ ቀደም ሲል ምንም ዓይነት መጠለያና የቤት ቁጥር ሳይኖራቸው በችግር ይኖሩ ለነበሩ በርካታ እናቶች ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች ተሰርተው የተሰጧቸው በመሆኑ የብዙዎችን ሕይወት በአጭር ጊዜ መለወጥ ችሏል።
አቶ ኑሪ መሀመድ የተባሉት የቀድሞው የፒያሳ ነዋሪ በበኩላቸው፣ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ እንደ ስሟ እውነተኛ አዲስ አበባ እንድትባልና የቱሪዝም ዋነኛ መዳረሻ እንድትሆን መነሻ የሆነው የኮሪደር ልማት መሆኑን ገልጸዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጃ እጅግ አስደናቂና ማራኪ በሆነ ዲዛይን የተገነባው መሠረተ-ልማት፣ መንግስት በተጨባጭ ውጤት ማሳየት የሚችልበትን ቁርጠኝነትና አቅም ለሕዝብ ያሳየበት እጅግ የሚያስደምም ተግባር መሆኑን ነዋሪዎቹ በአጽንኦት ገልጸዋል።
በመጨረሻም ይህንን ዘመን ተሻጋሪ የልማት አሻራ እና የተገኘውን ሰላምና ብልጽግና በባለቤትነት ስሜት ጠብቆ ለቀጣዩ ትውልድ ማስተላለፍ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ