AMN – ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

ተወዳደሪ የሆነ ስፖርተኛ ለማፍራት እና ጤናውን የጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠር ሰፊ የንቅናቄ ስራ መሰራቱን የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ።

የአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አሰግደው ኃይለጊዮርጊስ ከኤ ኤም ኤን ጋር ባደረጉት ቆይታ እንዳሉት፤ የስፖርት መሰረተ ልማቶችን ማስፋፋት በከተማዋ ልዩ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ ነው፡፡
መዲናዋን የስፖርት ቱሪዝም ማዕከል ማድረግ የሚቻለው ዓለም አቀፍ ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራዎችን በስፋትና በጥራት መከወንና ማሳካት ሲቻል ነውም ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ የስፖርት ማዘውተሪያ መሰረተ ልማት ስኬት ታዳጊዎች ስፖርታዊ ክህሎታቸውን የሚያሳድጉበት መሰረት መጣሉንም አንስተዋል፡፡
ቢሮው በተለይም የወጣቶችን ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማህበራዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ትኩረ አድርጎ መስራቱን የገለጹ ሲሆን ተወዳደሪ የሆነ ስፖርተኛ ከማፍራት አኳያ እንዲሁም ጤናውን የጠበቀ ማህበረሰብ ለመፍጠርም የተለያዩ የስፖርት ኢኒሼቲቮች ተቀረጸው ሲተገበሩ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡
የስፖርት ማዘውተሪያ ስፋራና ማዕከላት ግንባታም በሁሉም አካባቢዎች ፍትሃዊ በሆነ መንገድ እንዲሰሩ ለማድረግ ጥረት ሲደረግ እንደነበር አስረድተዋል፡፡

ማዕከላቱ ተተኪ ስፖርተኞችን ከማፍራት ባሻገር ዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እያስገኙ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው በበጎ ሥነ-ምግባር የታነጸ ዜጋን በማፍራትም ወጣቶችና ታዳጊዎች ጊዜያቸውን ከአልባሌ ስፍራ ማራቅ ያስቻለ ምኅዳር መፍጠሩን አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ዘመናዊና ደረጃቸውን የጠበቁ የስፖርት ማዘውተሪያዎችም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ውድድሮችን የምታስተናግድበት አቅም የፈጠሩ መሆናቸውንም ኃላፊው ተናግረዋል፡፡
በስፖርት ማዘውተሪያና ማሰልጠኛ ማዕከላት የሰለጠኑ ታዳጊዎች ወደተለያዩ ክለቦችና ብሔራዊ ቡድን ከፍተኛ የስፖርት ደረጃ እየተሸጋገሩ እንደሚገኝም አመላክተዋል፡፡
የሻምበል ምህረት