AMN- ሰኔ 7/2018 ዓ.ም

23ኛው የዓለም ዋንጫ ዛሬም ሲቀጥል አራት ጨዋታዎች ይከናወናሉ።
ጀርመን ከ ኩራሳኦ (ምሽት 2:00)
የመጀመሪያ ተሳትፎዋን የምታደርገው ኩራሳኦ ዓለምን ለማስደመም ተዘጋጅታለች።

ከተሳታፊ ሀገራት በቆዳ ስፋትም በሕዝብ ብዛትም ትንሿ ሀገር የሆነችው ኩራሳኦ በሰሜን አሜሪካ ዞን የማጣሪያ ውድድር ድንቅ ብቃት አሳይታ ነው ለታላቁ መድረክ የበቃችው።
ኩራሳኦ በዘንድሮው ዓለም ዋንጫ አንጋፋ በተባሉት የ78 ዓመቱ ኔዘርላንዳዊ ዲክ አድቮካት ይመራሉ።
በዓለም ዋንጫው 21ኛ ተሳትፎዋን የምታደርገው ጀርመን የዛሬውን ጨዋታ በቀላሉ ታሸንፋለች ተብሎ ይጠበቃል።
በተሳትፎ ብዛት በብራዚል ብቻ የምትበለጠው የአራት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ ጀርመን ያለፉት ሁለት የዓለም ዋንጫዎች ውጤት ደረጃዋን የሚመጥኑ አልነበሩም።

አውሮፓዊቷ ሀገር በ2018 እና 2022 የዓለም ዋንጫ ምድቧን እንኳን ማለፍ ተስኗት ነበር።
በወጣቱ አሰልጣኝ ጁሊያን ናግልስማን የምትመራው ጀርመን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ ኩራሳኦን በሁስተን ስታዲየም ትገጥማለች።
ኔዘርላንድስ ከ ጃፓን (ምሽት 5:00)
በዳላስ የሚደረገው የኔዘርላንድስ እና ጃፓን ጨዋታ ጥሩ ፉክክር ይደረግበታል ተብሎ ይጠበቃል።
12ኛ ተሳትፎዋን የምታደርገው ኔዘርላንድስ ሦስት ጊዜ ለፍፃሜ ብትቀርብም ዋንጫ ለማሸነፍ አልታደለችም።
በአሰልጣኝነት ዘመኑ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ብሔራዊ ቡድን የሚመራው ሮናልድ ኩመንም ዋንጫውን ያሳካል ተብሎ አይጠበቅም።
ለየትኛውም ብሔራዊ ቡድን ፈተና የመሆን አቅም ያላት ጃፓን ስምንተኛ ተከታታይ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ታደርጋለች።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የምሽቱ ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም በ2010 በተመሳሳይ በምድብ ተገናኝተው ኔዘርላንድስ 1ለ0 አሸንፋ ነበር።
ኮትዲቯር ከ ኢኳዶር (ለሊት 8:00 ሰዓት)
ሁለቱም ሀገራት በተሰጥኦ የተሞሉ በርካታ ተጫዋቾችን ይዘዋል። ኮትዲቯር ከተሳታፊ ሀገራት በዕድሜ ትንሹን ቡድን ይዛ ነው ለውድድሩ የበቃችው።
ወጣቶቹ አማድ ዲያሎ ፣ ያን ዲዮማንዴ እና ባዙማና ቱሬ የምዕራብ አፍራካዊቷ ሀገር ተስፋዎች ናቸው። በተለይ በማጣሪያው የነበራቸው ብቃት ተጋጣሚዎቿ ሊቋቋሙት የሚችሉት አልነበረም። በ15 የተለያዩ ተጫዋቾች 25 ግቦችን አስቆጥረው ነው ወደ ዓለም ዋንጫ ያለፉት።
ከ2014 በኋላ ወደ ታላቁ መድረክ የተመለሰችው ኮትዲቯር የዘንድሮ አራተኛ ተሳትፎዋ ነው።
ዊሊያን ፓቾ ፣ ሞይሰስ ካይሴዶ እና ፒየሮ ሂንካፒዬ የመሳሰሉ ኮከቦችን የያዘችው ኢኳዶር በማጣሪያው ድንቅ ነበረች።
በደቡብ አሜሪካ ሀገራት ማጣሪያ ከ18 ጨዋታ በአርጂንቲና እና ብራዚል ብቻ ነበር የተሸነፈችው። ከጨዋታዎቹ የተቆጠረባት አምስት ግብ ብቻ መሆኑ የተከላካይ ክፍሉ ጥንካሬን ያስመሰክራል።
በፊላደልፊያ የሚጫወቱት ኮትዲቯር እና ኢኳዶር የዛሬ ግንኙነታቸው በታሪክ የመጀመሪያው ነው።
ስዊድን ከ ቱኒዚያ (ለሊት 11:00)
ስዊድን 13ኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን ለማግኘት ፈታኝ መንገዶችን አልፋለች።
ቀጥታ ማለፍ ያልቻለችው ስዊድን በኔሽንስ ሊግ በነበራት ውጤት ባገኘችው ሌላ ዕድል ተጠቅማ ነው ወደ ዓለም ዋንጫው የተጓዘችው።
ለዚህም የቀድሞ የብራይተን አሰልጣኝ ግርሃም ፖተር ትልቁን ድርሻ ይወስዳል። አሰልጣኙ በውድድሩ ቀናቸው ከሆነ ለየትኛውም ተከላካይ ፈተና መሆን የሚችሉት ቪክቶር ዮኬሬሽ እና አሌክሳንደር ኢዛክ የሚጠቀምባቸውን መንገድ ለማየት በርካቶች ጓግተዋል።
ሰባተኛ የዓለም ዋንጫ ተሳትፎዋን የምታደርገው ቱኒዚያ ከምድቧ አልፋ አታውቅም።
ሰሜን አፍሪካዊቷ ሀገር ዘንድሮም አዲስ ታሪክ ለማስመዝገብ አቅም ያላት አትመስልም።
በሸዋንግዛው ግርማ